Thursday, 30 May 2013

አባይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መደበቂያ አይሆንም!


በስዊትዘርላንድ የሚገኙ የሲቪክ ተቋማት፣ የፖለቲካ ሃይሎችና፣ የዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ግብረ ሃይል የጋራ አቋም መግለጫ
በስዊዘርላንድ የምንገኝ የዕምነት ፣ የፖለቲካ እና የሲቪክ ማህበራት በጋራ በመሆን በሃገራችን ኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን አጠቃላይ የመብት ጥሰት እና ሃገርን የማውደም ዘመቻን በጋራ እንታገላለን።  በተለይም በአባይ ግድብ እና በሌሎች ግልጽነት እና ተአማኒነት በሌላቸው ልማቶች ስም የወገን ሃብት እና ንብረት ዘረፋ ይቁም የሚል ጥሪያችንንም እናቀርባለን።
እንደሚታወቀው በሃገራችን ኢትዮጵያ የመብት ጥሰቶች ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከቱ እና እየከፉ መጥተዋል።  ላለፉት 21 ዓመታት ሃገሪቷን በመግዛት ላይ ያለው ህውሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የሃገሪቱን ህገ-መንግስትም ይሁን ሃገሪቱ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ውሎችና ስምምነቶች ችላ በማለት በዜጎቹ ላይ ይህ ነው የማይባል የመብት ጥሰት እየፈጸመ ይገኛል።  የህዝቦች መብት እና ነጻነት በቅድምያ ሳይከበር በልማት ስም የሚደረግ ማንኛውም ተግባር ደግሞ ከየትኛውም ወንጀል ሁሉ የከፋ  ወንጀል ነው።  ሃገር ለህዝቦቿ የሰላም ከለላ እና መከታ ስትሆን እንጅ ህዝቦች ሰላማቸውን ፣ እረፍታቸውን ፣ መሸሸግያቸውን የሚነጠቁባት ፣ የሚገፈፉባት ፣ በስጋት እና በጭንቀት የሚኖሩባት ምድር ፈጽሞ መሆን የለባትም።  የሃገር ልማትም ሆነ እድገት ለህዝቦቿ እና ለዜጎቿ እንጂ ከቶም ለማንም ሌላ ፍጡር አይደለም።  መስረታዊ የሆነን የዜጎች መብት እንኳን ሳያከበር እና ሳያስከበር ፤ እጅግ የከፋ በደል በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለ ስርዓት ልማት ይቅደም በሚል ሽንገላ የሚደረግ ምዝበራ ተቀባይነት አይኖረውም።  የዜጎችን ሰብዓዊ-መብቶች ያላገናዘቡ የልማት ተግባራት ግብ እና ዓላማ የአፋኙን ስርዓት ጡንቻ ይበልጥ ለማፈርጠም እንጂ ፈጽሞ ልማት ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም።
በልማት ስም የሚተገበረው የኢህአዴግ ፖሊሲ በአንድ በኩል ሃገሪቱን ከማትወጣበት የብድር አረንቋ የሚከት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለተወሰኑ ብሄር ተወላጆች የማያልቅ የሃብት መዛቅያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።  ሃገሪቱ በሙስና ተጨማልቃ ፣ ዜጎች በኑሮ-ውድነት መከራቸውን እያዩ እና የሚላስ የሚቀመስ ባጡበት የኑሮ ሂደት ውስጥ ልማታችን ባለሁለት አሃዝ እድገት አሳየ እየተባለ የሚዘመረው ለፌዝ ካልሆነ እውነት ነው ብሎ ለመቀብል የሚቻል አይደለም።  በእርግጥ ሃገሪቱ ባለፉት ሃያ አመታት ብቻ ከሃምሳ ቢሊየን ዶላር በላይ በእርዳታ እና በብድር ማግኘቷን ስንመለከት ልማቷ አደገች ከሚባልለት አሀዝ በላይ መሆን በቻለ ነበር።  ሆኖም የተወሰኑ የስርዓቱ አቀንቃኞች የግል ኪሳቸውን ሲያደልቡበት የኢትዮጵያ ገበሬ ግን ማዳበርያ እንኳን ለመግዛት በሬውን ሽጦ ወይንም መሬቱን በከፊል በአራጣ አስይዞ ነው።  የሃገራችንን እድገት ለመለካት ውስብስብ ስሌትና ጠመዝማዛ መንገድ መሄድ አያስፈልገንም።  ከረሃቡ ጥናት በሚማሩበት ጠረጴዛ ላይ የሚያንቀላፉ ተማሪዎችን በአንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሄዶ ማየት ይበቃል ከዚህ ሌላ ኑሯቸውን የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ያደረጉ ቁጥራቸው ይህ ነው ተብሎ የማይገለጽ ከህጻን እስከ አዛውንት ያሉ ዜጎችን እንዲሁም ችግር ከቤታቸው ገፍትሮ በየመንገዱ ለልመና ያጋለጣቸውን አዛውንቶች እና አረጋውያን ማየቱ ለእድገታችን ምስክር ነው።
እንደ ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ሀቀኝነት (Global Financial Integrity) ድርጅት 2011 ዓመታዊ ዘገባ ከሃገሪቷ 11.7  ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከ2000 – 2009  ድረስ በ 10 ዓመታት ግዜ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ከሃገር መሸሹን ሲዘግብ ይህ መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በ2009 ብቻ 3.26 ቢሊየን ዶላር ከሃገር ኮብሏል ካለ ቡሃላ እጅግ የሚያስፈራው ደግሞ ሂደቱ ተባብሶ ቀጥሏል ማለቱ ነው።  ይህ ገንዘብ ተጨማሪ ልመና ሳያስፈልገው ሶስት የአባይ ግድቦችን ሊገድብ ይችል ነበር።  ወትሮስ የስርዓቱ ዓላማ መች ልማት ሆነ እና? አባይን በመገደብ ሃገርን የማልማት ፣ ዜጎችንም ከችግር የማውጣት ሳይሆን በልማት ስም የኢትዮጵያን ህዝብ ሃብት እና ንብረት ለመዝረፍ የተጠነሰሰ ሴራ ነውና ህዝባችን ስርዓቱ እያደረገ ያለውን ወንጀል በትክክል ሊያውቀው እና ሀይሉን አስተባብሮ ሊያስቆመውም ይገባል።
ፖለቲካ ሳይሆን ዓላማችን ልማት ነው በሚል ስልታዊ አካሄድ እና ብልጣብልጥ ቋንቋ የስርአቱ ታማኞች እና አገልጋዮች የአባይን ግድብ ቦንድ ለመሸጥ ከላይ ታች ሲሉ ይታያሉ።  ህዝቦች የተረጋጋ እና ሰላማዊ የሆነ ኑሮ መምራት የሚችሉበት ስርዓት ሳይኖር ልማት ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል እነዚህ አካላት ሊገነዘቡት ይገባል።  ቦንድ  ለመሸጥ እንደተሯሯጡት ሁሉ የህዝቦችን በደል ፣ ሃገሪቷ ላይ የነገሰውን ዘረኝነት ፣ ስርዓት አልበኝነት እና ሙስና ይቁም ለሚለው ቅድምያ እንዲሰጡ እንጠይቃቸዋለን።  የዚህ የገንዘብ ማሰባሰብ አንድ አካል መሆን በህዝቦች የመናገር ፣ የመደራጀት ፣ የመጻፍ ፣ የማምለክ ፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ በሃገር የመኖርን እና ሃብት የማፍራትን ነጻነት በመግፈፍ ላይ ላለ ስርዓት እገዛ ማድረግ በመሆኑ በታሰሩ እና እየታሰሩ ባሉት ፣ ከሃገር በሚሰደዱ እና በሚገደሉ ኢትዮጵያውያን ላይ በጋራ የግፍ በትር ካነሱት ጋር በቀጥታ መተባበር በመሆኑ ከእንደዚህ አይነት የወንጀል ተሳታፊነት እንዲታቀቡ ለማስገንዘብ እንወዳለን።  ዜጎቹን እያሰቃየ ላለ ስርዓት እድሜ ማራዘምያ እና ፖለቲካዊ ግብአት ለሚደረግ የገንዘብ ማሰባሰብያ ጥረት ተሳታፊ መሆን ታሪክ ተጠያቂ መሆን ነው።
በአባይ ወንዝ ላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ ያላትን መብት ማስጠበቅ ፣ አባይንም ይሁን አገሪቱ ያሏትን ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች በተገቢው ጥቅም ላይ በማዋል ህዝቧቿን ከድህነት ለማውጣትና ሃገሪቱን የማልማትና ለማበልጸግ በሚደረግ ጥረት ሁሉም የበኩልን ማበርከት እንዳለበት እናምናለን።  ሆኖም ግን አባይ እንዲገደብላቸው የምንሻላቸው ዜጎች ቅድሚያ በገዛ ሃገራቸው የመኖር ፣ ተዘዋውረው የመስራትና ሀብት የማፍራት ፣ የፖለቲካም ሆነ በሌሎች የህይዎት ዘርፎች በእኩልነት ተሳታፊ የመሆን ፣ የማሰብ እና ሀሳባቸውን በነጻ የመግለጽ ፤ የማምለክ ፣ የማመን ቅርሶቻቸውን የማስጠበቅ እንደዚሁም እምነታቸውን በነጻነት የመተግበር የማስፋፋት መብቶቻቸው በቅድሚያ ሊከበሩላቸው ይገባል።  ዛሬ የእስር-ቤት ቋንቋ ኦሮምኛ በሆነበት ሂደት ኦሮሞ ስለሆኑ ከየዩኒቨርስቲው የሚባረሩ ተማሪዎች ባሉበት ሃገር ፣ አስራ-ስምንት ወራት ድምጻችን ይሰማ በማለት ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ለሚያቀርቡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ምላሽ የግፍ እስር እና ግድያ በሆነበት ሂደት ፣ ብሄራቸው አማራ ስለሆኑ ብቻ ከየቅያቸው የሚፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎችን ማሰቃየት እና ማጉላላት እየተካሄደ ባለበት የዘረ ማጥፋት እና ማጽዳት ሂደት ፣ በአፋር ፣ በቤኒሻንጉል እንዲሁም በጋምቤላ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ በሙሉ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰት ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ድርሻችን መሆን ያለበት የዜጎች መብት ይከበር የሚለው ቅድምያ ሊሰጠው ይገባል።
ከግብ የሚደርስና ዘላቂነት የሚኖረው ልማት ሁሉን ያካተተ መሆን የሚጠበቅበት ሲሆን ግልጽነትም (transparency) ሊኖረው ይገባል።  ከዚህ አንጻር የአባይ ግድብ ገና ከአጀማመሩ ዓለም ዓቀፍ የጨረታ ስርዓትን (international tendering principles) ያልተከተለ ሆኖ እናገኘዋለን።  ያለጨረታ ኮንትራክት የተሰጠው የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ድርጅት ከዚህ በፊት በጊቤ ቁጥር-2 ስራ ላይ ተሳትፎ ስራዎችን ያበላሸ እና ከፍተኛ ወጪ ያስወጣ ድርጅት ነው።  ይህ ስራ ለእንደዚህ አይነት ድርጅት ሲሰጥ ማየት ዋናውን አላማ ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱ በተጨማሪ አሰራሩ በሙስና የተዘፈቀ መሆኑን እንዳንጠራጠር ያደርገናል።  ቅዲሚያ መከናወን የነበረባቸው የዲፕሎማሲና የቴክኒክ ስራዎች ሳይከናወኑ ወደ ስራ መግባት አንድም አገራችንን ወደ ጦርነት አውድማ ጎትቶ ማስገባት ሲሆን ሁለትም የሀገርን እና የህዝብን ንብረት ፣ ጉልበትና እውቀት ማራከስ ነው።  ከተባለው ዋና ተቋራጭ ድርጅት በተጨማሪ በቁሳቁስ አቅራቢነት የተሰለፉት ከአንድ ብሄር እና ክልል የተወጣጡ እንደ ኤፈርት ያሉ ድርጅቶች መሆናቸው ምን ያህል አድሎ እና ዘረኝነት የነገሰበት ሃገር እንደተመሰረተች የሚያሳይ ግልጽ ሂደት ነው።
በመጨረሻም በልማትም ስም ይሁን በሌላ ዘዴ በመጠቀም ሃገራችን እና ህዝቦቿን ያሏቸውን መልካም እሴቶች ለማጥፋት ፣ በሃይማኖቶች መሃከል ሳይቀር በመግባት ያለንን የህዝቦች ተከባብሮ ፣ ተሳስቦና ተቻችሎ የመኖር ዘይቤን አደጋ ላይ በሚከት መልኩ ስርዓቱ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በጥንቃቄ እንድንከታተል ፣ ለሃገራችን ሰላም መረጋጋት እና ብሎ ለቀጠናው መረጋጋት ሁላችንም በኢትዮጵያዊነት ወኔ እና ስሜት በአንድነት እንድንነሳ እንጠይቃለን። በመሆኑም በአባይ ስም በሀገር ውስጥ ካለው ምስኪን ሕዝብ ከወር ደመወዙ እንዲቆረጥ የሚደረገውንም ሆነ ከዲያስፖራው የሚሰበስበው ገንዘብ መብቶችን ለማፈን የካድሬዎችን ቁጥር ለመጨመር እና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለማፈን በቀጥታ ስለሚጠቀምበት በጋራ እንታገል።
አባይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መደበቂያ  የአምባገነኖች እድሜ ማራዘሚያ አይሆንም “!!!
ድል ለኢትዮጵያ!  ድል ለኢትዮጵያዊያን!

No comments:

Post a Comment