Monday, 24 June 2013

“አሜሪካ አቋማን የምትፈትሽበት ወቅት ላይ ናት” ክሪስ ስሚዝ


“አሜሪካ አቋማን የምትፈትሽበት ወቅት ላይ ናት” ክሪስ ስሚዝ

"አሸባሪነትን መዋጋት የግፍ ማከናወኛ ሽፋን አይሆንም"
gear 1
ኢህአዴግ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም ከአሜሪካ ጋር የመሰረተውን ግንኙነት አስታክኮ የሚፈጽመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ተገለጸ። አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ የምትመረምርበት ወቅት ላይ ትገኛለች ተባለ። ኢህአዴግ ጸረሽብርተኝነትን ለአፈናና ለበጀት ማሟያ እየተጠቀመበት እንደማይቀጥል ተመለከተ።
አሜሪካና ሌሎች ለሰብአዊ መብት መከበር ዋጋ የሚሰጡ አገሮች በሙሉ በ”አዲስ አበባው” አገዛዝ ላይ ጠንካራ አቋም መያዛቸውን ያለ አንዳች ማወላወል ማሳየት እንደሚገባቸው እንደራሴ (ኮንግረስማን) ክሪስ ስሚዝ ያስታወቁት ሽብርተኛነትን አስመልክቶ ጠንካራ ማሳሰቢያ በማስቀመጥ ነው።
እንደራሴ ስሚዝ የኢትዮጵያ ጉዳይ የተደመጠበትን የምክክር ሸንጎ ከዘጉ በኋላ በተለይ ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት “አሜሪካ በኢህአዴግ ላይ ያላትን አቋም የምትመረምርበት ወቅት ላይ ትገኛለች” ብለዋል።
አሜሪካ ከሰብአዊ ርዳታ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግና በተለይም ኢትዮጵያና አሜሪካ አሸባሪነትን በመዋጋት በኩል አብረው እንደሚሰሩ ያመለከቱት እንደራሴው፣ “ሽብርንና ሽብርተኛነትን የመታገል ትብብር ግን የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመርገጥ ፍቃድ ማግኛ አይደለም። የመብት ረገጣ ሽፋን ሊሆን አይገባም” በማለት የኢህአዴግና የመሪዎቹን ተግባር ኮንነዋል።
“አንድ አገር ገና ለገና ሽብርተኛነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጎን ስለቆመ ብቻ የህዝብ ሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ አተገባበር ላይ ዝም ሊባል አይገባም” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ስሚዝ፣ ሽብርን መዋጋት የኢትዮጵያ የራስዋም ፍላጎት አንደሆነ አመልክተዋል።
“ስለዚህ” አሉ ክሪስ ስሚዝ፣ “ስለዚህ የአሜሪካ መንግስትም ሆነ ሌሎች የምራብ አገራት፣ ኢህአዴግ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ተግባር በመረዳት አቋማቸውን በግልጽ ማስቀመጥ ይገባቸዋል”
“ለሰብአዊ መብት መከበር ዋጋ የሚሰጡ አገሮች በአዲስ አበባው መንግስት ላይ የማያወላውል ጠንካራ አቋም መያዛቸውን ማሳየት አለባቸው” ሲሉ የተደመጡት ክሪስ ስሚዝ “ከዚህ ቀደም አርቅቄ፣ አስተዋውቄ፣ ለውይይት አቅርቤው የነበረውን ኤች አር 2003 ህግ እንደገና በማሻሻል ለድምጽ አቀርበዋለሁ” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ህገደንብ” የሚል ስያሜ ያለው ህግ፣ ኢትዮጵያን የሚመራው ኢህአዴግ ከአሜሪካ መንግስት ለሚፈልገው ማናቸውም ድጋፍ መሟላት የሚገባቸውን የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብት ግብአቶችን በቅድመ ሁኔታ የሚያስቀምጥ ነው። እንደራሴ ክሪስ እንደገና ለድምጽ እንደሚያቀርቡት ደጋግመው የገለጹት ይህ ህግ ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ አፍስሶ በአሜሪካን ጎትጓቾች (ሎቢዪስቶች) ዘመቻ ያካሄደበት ነው።
መለስን ”አሮጋንት/ዕብሪተኛ/“ በመለት የገለጹት ክሪስ ስሚዝ “ከመለስ ሞት በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ታመራለች” የሚል እምነት እንደነበራቸው በመናገር “የሰማሁት ምስክርነት ከዚህ የተለየ፣ ተስፋ ከተደረገው ተቃራኒ ነው” ብለዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ “ብዙዎች” ሲሉ በጥንቃቄ የገለጹዋቸው አካላት ከመለስ ሞት በኋላ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ መንግድ ታመራለች የሚል እምነት እንደነበራቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። በውል የተየው ነገር ኢትዮጵያዊያን ወደ ባሰበት ችግርና የመብት ረገጣ የመዘዋወራቸው ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህም አሳሳቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በማብቂያቸውም “አሁን ፖሊሲያችንን ዳግም የመፈተሽያ ጊዜ ላይ ነን። ቁም ነገሩ ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር መቆሙ ላይ ነው። ከተጨቆኑት ወገኖች ጋር እንቆማለን” የሚል ከተለመደው የአሜሪካ አቋም የተለየ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የተገኙበትን የምክክር ሸንጎ ተከትሎ እስካሁን ድረስ የኢህአዴግ አቋምና ምላሽ አልታወቀም። ይሁን እንጂ ቀደምሲል ኤች አር 2003 ህግ ሆኖ እንዳይጸድቅ ኢህአዴግና ወዳጅ ባለሃብቶች ተመሳሳይ ተግባር ለማከናወን ሩጫ መጀመራቸው ተሰምቷል። በተጨማሪም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲፕሎማሲ ጅምናስቲክ መጀመሩ ታውቋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተለያየ ወቅት መለስ በሽብርተኛ ትግል ሰበብ አሜሪካንንና የምዕራቡን ዓለም እያምታቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል። ሆን ተብሎ በተሽከርካሪዎች ላይ የተቀነባበረ የፈንጂ ማፈንዳት፣ ህዝብን የማሸበር ተግባር እንደሚፈጸም በማመልከት ተቃዋሚዎች ሲጮሁ ሰሚ አልነበራቸውም። የሹልክዓምድ (ዊኪሊክስ) መረጃ ይህንኑ ይፋ ማድረጉና ኢህአዴግ ራሱ ፈንጂ አፈንድቶ “አሸባሪዎች ፈንጂ አፈነዱ” በሚል እንደሚያምታታ ማጋለጡ ይታወሳል።
አቶ መለስ አሜሪካና ምዕራባዊያን ሰብአዊ መብትን፣ ምርጫንና የዲሞክራሲ መብቶችን አስመልክቶ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው “ጦራችንን ከሶማሊያ እናስወጣለን፣ ቀጠናው ቢተራመስ ተጠያቂ አይደለንም” የሚል ምላሽ  እየሰጡ ያስፈራሩ እንደነበር የሚጠቁሙ የጎልጉል ምንጮች “ኢህአዴግ ብር ሲፈልግና ካዝናው ሲጎድል ዘወትር የሚያነሳው የሽብርና አሸባሪዎችን የመታገል ውለታ ድርጎ ነው” ብለዋል። በ1997 ምርጫ ወቅት የተሸነፈው ኢህአዴግ በወቅቱ አሜሪካን ጫና ልታደርግ ስትሞክር “ሰራዊታችንን ይዘን ወደ ክልላችን እንገባለን። ተቃዋሚዎች ጦር የላቸውም። በቀጣናው ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ አይደለንም” በማለት አቶ መለስ አሜሪካን ጫናዋን አቁማ ከህወሃት ጎን እንድትቆም ማድረጋቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆነ ይናገራሉ። ያም ሆነ ይህ እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ ኢህአዴግ የውጪውን ዓለም የሚጋልብበትን የፖለቲካ “ጆከሩን” ወይም “ሽብርን መታገል” መርጠው ” ካሁን በኋላ በዚህ ሂሳብ መጫወት አይቻልም” ማለታቸው ቀጣዩን የፖለቲካ ጨዋታ እንደሚያከረው ተገምቷል።(Source: http://www.goolgule.com)

Tuesday, 11 June 2013

ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው? "በሩ ይከፈት፣ በአባይ ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ"


ኢህአዴግ ጣና በለስን ለምን አፈራረሰው?

"በሩ ይከፈት፣ በአባይ ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ"
BELES inlet
በግብጽ ረዳትነት፣ በሱዳን መሪነት መንግስት ለመሆን የበቃው ህወሃት/ኢህአዴግ ግዙፉን የጣና በለስ ፕሮጀክትና ንብረቱ እንዲዘረፍ ያደረገበትን ምክንያት በማንሳት መከራከር እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ። የግብጽ ፕሬዚዳንት ሙርሲ እንዳደረጉት በአገር ጉዳይ ሁሉንም ያሳተፈ ግልጽ አቋም እንዲያዝና አጋጣሚውን በመጠቀም ብሔራዊ ህብረት እንዲፈጠር ኢህአዴግ በሩን ሊከፍት እንደሚገባ ተገለጸ።
በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ በማሳሰብ ለጎልጉል አስተያየት የሚሰጡት የኢህአዴግ ሰው እንዳሉት በርካታ ጉዶች ያሉበትን የአባይን ግድብ ተከትሎ ከግብጽ ጋር የተነሳው ውዝግብ አስቀድሞ የሚታወቅ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ስልትና ውጤት ነው።
አሁን ድረስ አገር እየመራ በነጻ አውጪ ስም የሚጠራው ህወሃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ “ዲሞክራሲ አመጣሁ” በማለት ኢትዮጵያን መምራት እንደጀመረ የሚያወሱት የኢህአዴግ ሰው፤ አቶ መለስ ብቻቸውን ይነዱት የነበረው ኢህአዴግ እንደፈለገ ቆዳውን እየቀያየረ የተጠቀመበትንና በእስስት በመመሰል “ከሽፏል የሚሉትን” ስልት ያብራራሉ።
በዲሞክራሲ ስም የተጀመረው የኢህአዴግ አገዛዝ ቆየት ብሎ “ልማታዊ ነኝ፣ ልማት ግቡን የሚመታው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቀመር ነው” በማለት ፕሮፓጋንዳውን አሰፋ። የልማት ህልመኛነቱ ሲነቃበት “የትራንስፎርሜሽን ዘመቻ” በማለት አዲስ የፕሮፓጋንዳ እቅድ ነድፎ ህዝብና አገር ሲያታልል ቆየ። ይህም አላራምድና በህዝብ የመታመን ድል ሊያስገኝለት እንደማይችል ሲታመን “የህዳሴያችን ግድብ” ተብሎ አባይ አጀንዳ እንደተደረገ ያመለከቱት ዲፕሎማት፤ “ኢህአዴግ አገር ውስጥ የሚያምታታባቸው መንገዶች ሲጠናቀቁበት የፕሮፓጋንዳውን ዘመቻ አንድ ደረጃ ከፍ አደርገው” በማለት አሁን ከግብጽ ጋር ስለተጀመረው ውዝግብ አስተያየታቸውን ይጀምራሉ።
አባይን በመገደብ ኢትዮጵያን በልማት ለማሳደግ እየተጋ እንደሆነ የሚናገረው ኢህአዴግ፤ አስቀድሞ በመላው የብአዴን የበታች አመራሮችና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ቂም ስላስቋጠረው የጣና በለስ ሰፊ ፕሮጀክት ዝርፊያና ውድመት የጠራ መልስ ሊሰጥ እንደሚገባ ዲፕሎማቱ ይናገራሉ።
በጣሊያን መንግስት ሙሉ ድጋፍ አባይ ወንዝን መሰረት አድርጎ የተገነባውን የጣና በለስ ፕሮጀክት ህዝብ እያየ አፈራርሰው እንደወሰዱት፣ የተዘረፈው ንብረት ወደ ኤርትራ እንዲጓጓዝ መደረጉን ያመለከቱት እኚሁ ሰው፣ “ጣና በለስን አፈራርሶ ያስዘረፈ ፓርቲና አመራሮቹ አሁን አባይን ለመገደብ የተነሱበት መነሻ ለአብዛኛው የኢህአዴግ አባላት እንቆቅልሽ ነው” ባይ ናቸው። በማያያዝም በወቅቱ ዝርፊያው ሲካሄድ ህዝብ አካፋና ዶማ በመያዝ “ንብረቱ አይዘረፍም” በማለት መንገድ በመዝጋቱ ዝርፊያው በሌሊት እንዲካሄድ ያደረገ ድርጅት እንዴትስ ይታመናል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።
“ኢህአዴግ የህይወት ዘመኑ የሚጠናቀቅበት ጠርዝ ላይ ስለሚገኝ፣ በአባይ ጉዳይ አመካኝቶ ህዝባዊ ማዕበል ለማቀጣጠል አቅዷል። የአባይ ጉዳይ ከዚህ የተለየ ተግባርና ዓላማ የለውም” የሚሉት አስተያየት ሰጪ፣ የጣና በለስ ፕሮጀክት እንዲወድም መመሪያ የተሰጠው ከግብጽ እንደነበር መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ቀንደኛ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽ አባይ ላይ የሞትና የህይወት አቋም ቢኖራትም አሁን የተጀመረው ውዝግብ ከወሬ የዘለለ ግጭት እንደማያስነሳም ተናግረዋል።
በግብጽ አሁን ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት ለማስቀየር እየሰሩ ያሉት ፕሬዚዳንት ሙርሲ፣ የአባይን ጉዳይ ልቡን ከነፈጋቸው የአገራቸው ህዝብ ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ እንደሚጠቀሙበት ያመለከቱት አስተያየት ሰጪ፣ የአገራችን ተቃዋሚዎች እንደ ግብጽ ተቃዋሚዎች መጫወቻ እንዳይሆኑ ይመክራሉ። “ኢህአዴግ የሚቃወሙትን ፓርቲዎች አባይን ተንተርሶ በአገር ክህደትና የአገርን ብሔራዊ ጥቅምን በመጻረር ፈርጆ ከህዝብ ጋር ሊያጋጫቸው ተዘጋጅቷልና ከወዲሁ ዝግጅት አድርጉ” ሲሉ ይመክራሉ።
በሌላ በኩል ሙርሲ እንዳደረጉት ኢህአዴግ በወቅቱ ጉዳይ ላይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሊያነጋግር እንደሚገባ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል ተናግረዋል።
አቶ ኦባንግ እንደሚሉት “አገር የህዝብ ነው። ህዝብ በተለያየ መልኩ ይወከላል። ከሚወከልበት መንገድ አንዱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው። አገርን አስመልክቶ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ወኪሎችን ማግለል ህዝብን የማግለል ያህል ነው። ይህን ማድረግ ይቅር የማይባል ወንጀል ይሆናል”
አገር ቤት ያሉትን ብቻ ሳይሆን በውጪ አገር ያሉትንም ፓርቲና ድርጅቶች በዚህ ጉዳይ ማነጋገር ግድ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ለዚህ አገራዊ ውይይት ማንኛውም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ አይገባም” ብለዋል።
አጋጣሚው ለምንናፍቀውና ሁሉንም የአገሪቱን ህዝብ በእኩል ደረጃ ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት ለመፍጠር እንደሚረዳ አቶ ኦባንግ ጠቁመዋል። የተለየ አመለካከት በማራመዳቸው ብቻ ዜጎችን እስር ቤት በማጎር እስከ ወዲያኛው መዝለቅ እንደማይቻል ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የውይይት በር በመክፈት የማያልፍ ታሪክ ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል።
“ሙስሊም ወንድሞች ፍትህ የጠማቸው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ የሚያረጋግጡበትን መድረክ አቶ ሃይለማርያም በማመቻቸት የማይረሳ ታሪክ ሊሰሩ ይገባል” በማለት ጥሪ ያስተላለፉት አቶ ኦባንግ “አገር የህወሃት አይደለችም፤ አገር የኢህአዴግ አይደለችም፣ አገር የግለሰቦች አይደለችም። አገር የሁሉም ነው። ባገር ጉዳይ ባይተዋር ሊደረጉ የሚገባቸው ዜጎች ሊኖሩ አይገባም። ኢህአዴግ ይህን ጉዳይ ሊያስብበትና በሩን ለእርቅና ለውይይት በመክፈት ህዝብንና ራሱን ተጠቃሚ ሊያደርግ ይገባል” ብለዋል።
“ባድመ በተወረረች ጊዜ የተፈጠረው ህብረት በስተመጨረሻ በክህደት መጠናቀቁ፣ በዜጎች አጥንትና ደም ላይ የአገር ብሔራዊ ጥቅም ተላልፎ እንዲሰጥ መደረጉና በበርካታ ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች ኢህአዴግ በህዝብና በአባላቱ ጭምር እምነት ያጣ ፓርቲ ነው” በማለት ኢትዮጵያ የከፋ ችግር ቢያጋጥማት እንዴት ልትቋቋም ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላቸው አቶ ኦባንግ አመልክተዋል።
ስርዓቱ በየደረጃው በችግር የተተበተበና በህዝብ የማይታመን፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችን እስር ቤት ያጎረ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ቂም የተቋጠረበት፣ ፍትህና ርትዕ የተጓደለባቸው ያዘኑበት፣ በየአቅጣጫው ጠላት ያከማቸ፣ አገርን የሚፈትን አደጋ ቢፈጠር ህዝብን አስተባብሮ አደጋውን ለመመከት የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን የገለጹት አቶ ኦባንግ “ኢህአዴግ አጋጣሚውን አሁንም ሊጠቀምበት ይገባል” ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ኦባንግ የሰማያዊ ፓርቲ ያስተባበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ ኢህአዴግ ክስ ለመመስረትና ዜጎችን ለማሰር እያደረገ ያለውን ዝግጅት በመቃወም ሰሞኑን ለአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል። ከደብዳቤያቸው በተጨማሪ ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር ኢህአዴግ ዜጎችን ከማሰሩ በፊት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ መደረሱን ጨምረው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የአባይ ግድብን አስመልክቶ በከፍተኛ ደረጃ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ግብጽ መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ በርካታ አስተያየትና ትንተና እየቀረበበት ነው። ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት አያመሩም፤ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከመጠቀም ውጪ ሌላ አጀንዳ የላቸውም የሚሉ ያሉትን ያህል ግብጽ በጦር አቅሟ ያላትን የበላይነት በማመልክት ባልታሰበ ሰዓት ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀቷን የሚያትቱም በርካታ ናቸው።
የግብጽ ፕሬዚዳንት ከተቃዋሚዎች ጋር ያደረጉትና ይፋ የተለቀቀው ቪዲዮ ላይ “ተቃዋሚዎችን በመርዳት ኢትዮጵያን ማተራመስ፣ ኢትዮጵያን መደብደብ ነው … ” በማለት ሲዝቱ የነበሩት ጽንፈኛ ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት የከረረ ቃላት ሲወረውሩ ሰንብተዋል። ኢትዮጵያም በበኩሏ የግብጽን አምባሳደር በማስጠራት ማብራሪያ እንዲሰጣትና በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ ማዘዟን ይፋ አድርጋለች።
ግብጽ በችግር መተብተቧን፣ የሶማሌ መበታተንና፣ የሱዳን ሁለት አገር መሆን፣ የኤርትራ መሽመድመድ ኢትዮጵያን በቀጠናው ጉልበት ያላት አገር አድርጓታል የሚሉ ተንታኞች በበኩላቸው ግብጽ ወደ ጦርነት እንደማታመራ ሰፊ መከራከሪያ በማቅረብ ይናገራሉ። ከግድቡ ግንባታ ጀርባ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ አገሮች እጅ እንዳለበትም የሚጠቁሙ ዘገባዎች በየፊናው ተሰራጭተዋል።
“ኤርትራ ተነፈሰች” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ግብጽ ተቃዋሚዎችን ለመርዳት ከተንቀሳቀሰች ኤርትራ ርዳታውን በማከፋፈልና ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ አገር እንድትሆን ስለማትፈልግ በችግሩ ዙሪያ ቤንዚን ለማርከፍከፍ አጋጣሚው እንደሚመቻችላት ያስረዳሉ። የአረብ ሊግ የክብር አባል የሆነችው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጋር በተያያዘ በበርካታ ጉዳዮች የምትታማ አገር እንደሆነች የሚታወስ ነው።
ዘግይታ “እኔ ከግብጽ የተለየ አቋም ነው ያለኝ” በማለት የገለልተኛነት ስሜት እንዳላት ይፋ በማድረግ ለግብጽ የድጋፍ ጥሪ መልስ የሰጠችው ሱዳን እንደማትታመን የሚግለጹ ደግሞ “አቶ መለስ ደቡበን ሱዳን ላይ ሲከተሉ በነበረው አቋምና ደቡብ ሱዳን እንድትገነጠል በመናደረጓ ሱዳን አቂማለች” ይላሉ፡፡ እንደነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ምንም ይሁን ምን በአገር ውስጥ ያለውን ችግር በውይይት በመፍታት ብሔራዊ አንድነትና ህብረትን ማጠናከሩ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊዋ ነው። ስለዚህ “በር ይከፈት በአባይ ጉዳይ አገራዊ አቋም እንያዝ” የሚለው የአቶ ኦባንግ ብቻ ጥያቄ አይደለም።

Monday, 10 June 2013

ድንቁርና የሚድንም የማይድንም ሕመም ሊሆን ይችላል (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)


ድንቁርና የሚድንም የማይድንም ሕመም ሊሆን ይችላል (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም
ከጥቂት ቀናት በፊት አንዳንድ ሰዎች በዓባይ ጉዳይ ቀረርቶና ሽለላ ማሰማት ሲጀምሩ ከባድ የሆነ የመረጃ እጥረት መኖሩን ስለተገነዘብሁ ስለግብጽ የኃይል ሚዛን ደረቅ መረጃ የጦርነትን መጥፎ መልክ ከሚገልጽ አስተያየት ጋር አቀረብሁ፤ የወያኔ ሎሌዎች ወዲያው በእኔ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ከፈቱ፤ ድንቁርናው ከዚህ ይጀምራል፤ ማሪዮ ፊልሞና ብሩኖ ‹‹በአፍራሽ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዛሬም የግብጽን ጦር ገና ከሩቁ እንድንገብርለት ጉትጎታ ይዘዋል፡፡›› በማለት ውርጅብኙን ይጀምራል፤ አንድም ቦታ እኔ ያቀረብሁትን መረጃም ሆነ አስተያየት አንሥቶ ጉድለትን አላሳየም፤ ዓላማው መረጃው ወይም አስተያየቱ አይደለም፤ ለረጅም ጽሑፉ ዓላማው እኔ ነኝ፤ የአሉላ ሰሎሞን ጆቫኒ የግጥም ዓይነት መልክ ከመያዙ በቀር ያው ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam
ለእነዚህ ሰዎች መልስ የሚያስፈልጋቸው በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ለማረም አይደለም፤ አንዳንድ ሰዎች መልስ አይገባቸውም ይሉኛል፤ እውነት ነው፤ እኔ በሥራዬ እቆማለሁ፤ ወይም በሥራዬ እወድቃለሁ፤ ነገር ግን ንጹሐን ወጣቶችን አዋቂዎች መስለው እንዳይበክሉ መከላከል ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ድንቁርና እንደተላላፊ በሽታ ነው፤ ይጋባል፡፡
ድንቁርና መጥፎነቱና አደገኛነቱ ከኋላውም ሆነ ከፊቱ የሚያይበት ዘዴ አለመኖሩ ነው፤ ለዛሬ፣ ለሆድ ብቻ መኖርን ዕለታዊ ዓላማው የሚያደርግ ነው፤ አንጎሉ በድንቁርና የተሞላ ለምንም ሌላ ነገር ቦታ የለውም፤ ይህ ድፍን ወይም ፍጹም ድንቁርና ነው፤ ተስፋ-ቢስ ነው፤ አንጎሉ ውስጥ ድንቁርና ያልደረሰበት ትንሽ ቦታም ቢሆን ከአለ የእውቀትን ዘር ለመዝራትና ብርሃን ለመፈንጠቅ ዕድል ይኖራል፤ አለዚያ ድቅድቅ ጨለማ ነው፡፡
ፊልሞን በሚል ስም ራሱን የሚጠራው ከሽፍንፍን መውጣት ያልቻለው ፈሪ ፊደልን ብቻ የተማረ መሀይም ነው፤ ይህንን አንብበህ መልስ ስጥበት ብሎ ያዘዘው ሰው የእኔን ጽሑፍ ካልሰጠው በቀር የእኔ ስም ባለበት ሰሌዳ ደርሶ ከሆነ ሰውዬው የማየት ችግርም አለበት ማለት ነው፤ በሰሌዳው መጀመሪያ ገጽ ላይ የእኔ መጽሐፎች ሽፋኖች ይታያሉ የሎሌነቱን ተግባር ለመፈጸም የቀባጠረውን በዝምታ ማለፍ እሱን ራሱንም ሆነ በተለይም የአነበቡትን ሰዎች መጉዳት ሰለመሰለኝ ከእውነቱ ጋር እንዲጋፈጥ ማስገደድ ይገባኛል፤ ባንዳውን ምሁር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስን ማወቁን ሳደንቅለት ኃይለ ሥላሴ ጉግሳንና ጭፍሮቹን እንዳልረሳቸው ተስፋ አለኝ፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከእርሳቸው በበለጠ የጦርነትን ምንነት ጠንቅቆ የሚረዳ እና የጦርነትን አስከፊነት እንደክቡርነታቸው በቴሌቪዥን ሳይሆን በተግባር የሚረዳ ይመስለኛል:: እናም የሃገራችን ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ስራ ከጎን ከመቆም ይልቅ በተንኮላቸው የማይወዱትን አካል ጠልፎ ለመጣል እስከጠቀመ ድረስ የሃገርን ጥቅም ለመሸጥ ጉጉነታቸውን አይቸበታለሁ፡፡
ይህንን ለመጻፍ የሚያስችል ድንቁርና ፍጹም ነው፤ ይህንን ፍጹምነት ሲያጠናክረው፤ –
ሰውየው እኮ ሃገራችን በደም አንባ ስትታጠብ በርሃብ አለንጋ ስትገረፍና ህዝቦቿ በአለም አደባባይ ስንዋረድ የኬንያዊውን የመሃመድ አሚንን ያክል ለሃገራችን ያላበረከቱ ግለሰብ ናቸው:: ዜጎች ያለፍርድ ሲረሸኑ ሲዋረዱ ሃገራችን የጨለማ ዘመን አገዛዘን እያማከሩ ሲሰሩ የነበሩ ሰው ስለሃገር ክብርና ስለሃገር እድገት ብዙም ይገዳችዋል ብሎ መጠበቅ ከሰማይ ደመናን እንደመዝገን ይሆናል::ተማሪወቻቸው እና ከሳቸው በእጅጉ በትምህርት እና በእድሜ የሚያንሱ ወጣቶች ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው ነጻነት ሲዋደቁ ክቡርነታቸው ግን ለንደን እና ዋሽንግተን እየተንሸራሸሩ በነበረበት ወቅት በርሃብ እና በጦርነት እየነደደ ስለነበረው ህዝባቸው አንዲትም ቃል እንደተነፈሱ ታሪክ የላቸውም ::
የተማሪ ቤት ግቢን የረገጠ ይህንን አይጽፍም፤ አንደአለቆቹ መሸጦ አስተማሪ ቤቱ ድረስ እየሄደ ፊደል ያስቆጠረው ሳይሆን አይቀርም፤ ፊደሉን ማወቁን እንደመጨረሻ ትምህርት ወስዶታል፤ በአንድ በኩል የሚያሳዝን ሰው ነው፤ በሌላ በኩል ግን ድፍረቱ ድንቁርናን የሚያበረታና ለጥቃት የሚዳርግ ነው፤ ለኮሎኔል መንግሥቱ ጂቡቲ ጦርነት ብትከፍት ኢትዮጵያ እንደማታሸንፍ ነግሬው ነበር፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የክምችት ክፍል ሄዶ በጓደኞቹ እርዳታ ትንሽ ቢቆፍር በደርግ ዘመን ‹‹ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነዋል፤›› በማለት የተናገርሁትን ያገኘውና ዓይኑን ይከፍትለት ነበር፤ ምስክሮቹ ሁሉ በሕይወት ባሉበት ጊዜ እንዲህ ያለ ውንጀላ አያዋጣም፤ ወይም እኔን በባንዳነት ከራሱ ጋር ሊያዛምደኝ ፈልጎ ከሆነ ያማ መንገድ አያስሄድም፤ እግዚአብሔር ይመስገንና በዚህም በዚያም ከባንዳ ጋር ንክኪ የለኝም፡፡
እኔ ስለጦርነት የጻፍሁት ለሚያውቁና ማሰብ ለሚችሉ ሰዎች ነበር፤ የሚያውቁ ሰዎች የምላቸው የአሥራ ዘጠነኛውን የመጀመሪያ አጋማሽና የሃያ አንደኛውን ምዕተ-ዓመታት ሁኔታዎች ተገንዝቦ ማመዛዘን የሚችለውን፣ በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ የተቀዳጀችውን ድል በኩራት እያስታወሰ በሃያኛው ምዕተ-ዓመት ደግሞ በማይጨው ላይ በኢጣልያ ጦር የተሸነፈችበትን ውርደት የሚያውቅና የሚሰማው፣ በዚያው ላይ ኢጣልያ በአድዋ መሸነፍ የተማረች ስትሆን ኢትዮጵያ በአድዋ ድልም ሆነ በማይጨው መሸነፍ ሳትማር መቆየቷን የሚያውቅና የሚቆረቆር፣ ካላወቀም ለማወቅ የሚጓጓ ሰው ነው፤ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ከወያኔ ጀሌ ጋር፣ ከሻቢያ ጀሌ ጋር፣ ከሶማልያ ጋር፣ በቅርቡም ከኤርትራ ጋር፣ በኋላም ከሶማልያ አክራሪዎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ የሚያኮራ ነገር አልታየም፤ ይህንን ሁሉ እውነት አውቆና አመዛዝኖ ለማየት የማሰብ ችሎታን ይጠይቃል፤ ማሪዮ ፊልሞና ለዚህ አልታደለም፤ በቅዠት ዓለም ውስጥ ሆኖ ራሱን አሉላ የሚለው ብሩኖም እንዲሁ ያልታደለ ሎሌ ነው፤ ለሁለቱም ከጉራዕና ከጉንደት በኋላ ታሪክ የለም፤ እዚያ ላይ ቆሟል፤ የደበዘዙ ዓይኖችና የደነዘዙ አንጎሎች በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የሆነውን ይዘው 2005ን ለመደልደል የሚፈልጉ እንደፊልሞንና እንደአሉላ ሶሎሞን ያሉ ምስኪኖች እንዳይታዘንላቸው ትዕቢታቸው አያስቀርብም፤ እንዳይተዋቸው መርዛቸው ብዙ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፤ ያለው አማራጭ ድንቁርናቸውን ማጋለጥ ብቻ ነው፡፡
የታሪክ ዋናው ዓላማ ጥቅም ዓይኖችን በአለፈው ነገር ላይ ተክሎ ወደኋላ ለማየት ሳይሆን ከፊታችን የተደቀነውን የዛሬውን ችግር ለመወጣት ከአለፈው ስሕተት መማር ነው፤ አንድ ጥያቄ፡– የኢትዮጵያ ድንበር ከዓባይ ጀምሮ ወደሰሜን እየሰለለ የሄደው ለምንድን ነው? እነፊልሞንና እነአሉላ ሶሎሞን ይህንን የማስተዋል ብቃት የላቸውም፤ ቢያስተውሉትም ስለማያስቡ አያሳስባቸውም፤ ማሰብ ቢችሉ የሚደነፉበትንና ግጥም የሚጽፉበትን ወደእፍረት ይለውጥባቸው ነበር፤ በቅርቡም በባድመ ጦርነት ፉከራውና ሽለላው ወደእፍረት ሲለወጥ አይተናል፤ ድንቁርና የሚደነድነው እውነትን፣ ከእውነት ጋርም እውቀትን እያፈነ ነው፡፡
በ1864 ዓ.ም. አካባቢ በጦርና በጋሻ አሸንፈናል፤ ዛሬም በ2005 ዓ.ም. በዚያው ዘዴ እናሸንፋለን ማለት የድንቁርና ዘውድ ነው፤ እኛ እንዳልተለወጥን ሌሎችም አልተለወጡምና በ1988 ዓ.ም. በአድዋ ኢጣልያን ድባቅ መተናል፤ እያልን ስንፎክር በ1928 ተመልሶ ሲመጣ በማይጨው ድባቅ መታን፤ ያን ጊዜ የሆነውን ማን ነው ከታሪክ የተማረው? ዛሬ ኢጣልያ ቢመጣ ፊልሞንና አሉላ ከነጓደኞቻቸው መንገድ መሪዎች መሆናቸው እጅግም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም እኔ የግብጽን ኃይል ለማሳወቅ የፈለግሁት እንዳንዘናጋ ሲሆን የእነማሪ ፊልሞንና አሉላ ጆቫኒ ፍላጎት ደግሞ ለማዘናጋት መሆኑ ነው፤ ዋናው ጥያቄ ግን ለምን እንድንዘናጋ ይፈልጋሉ? የኢትዮጵያ መዘናጋትና ለአደጋ መጋለጥ ምን ይጠቅማቸዋል? የሚለው ነው፤ መልሱ ውስጥ አልገባም፤ ፡፡
ዘመኑ እውቀት የረከሰበት ነው፤ ዛሬ አንድ ሰው የፈለገውን እውቀት ለማግኘት ከስንፍናና ከእኩይ ትዕቢት በቀር የሚያግደው የለም፤ በድንቁርና ከመኩራራት ፈርጠም ብሎ በእውቀት መስተካከልና ለወደፊቱ ማሰብ ቀና ይሆናል፤ ድንቁርናን የሚድን ሕመም እናድርገው፡፡