Saturday, 17 November 2012

“ጥቁሩ ሰው” ይናገራል! አቶ ኦቦንግ ሜቶ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

“ጥቁሩ ሰው” ይናገራል!

Obang O Metho
“ጥቁሩ ሰው” ይሉታል። ኢትዮጵያዊያን ለሚያሽከረከራት አስፈሪ ፈተና መፍትሄው ሰብአዊነትን ማስቀደም ብቻ ነው የሚል የጸና እምነት አለው። “ከጎሳ በፊት ሰብዓዊነት” በሚል መሪ ዓላማ ከሚመስሉት ጋር በመሆን ድርጅት አቋቁሞ መሥራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባከናወናቸው ሥራዎች ከፍተኛ እርካታ እንደሚሰማው ያምናል። ኢትዮጵያዊያን ችግር ደርሶባቸዋል በሚባልበት ሁሉ ቀድሞ ደራሽ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በዚህና በሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሰራቸው ስራዎቹ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችና አድናቂዎች ለማፍራት ቢችልም “ከጀርባው ድብቅ ዓላማና አጀንዳ አለው፣ ብቻውን ይሮጣል” የሚሉትን ጨምሮ በግል አቋሞቹ ዙሪያ ነቀፌታ የሚሰነዝሩበትም አሉ።
የወደፊት ዕቅዱና የሚነቅፉት እንደሚሉት መቼ ፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ ይፋ ያደርጋል? በሚሉትና በተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ ኦባንግ ሜቶ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። ኦባንግ ሜቶ (ጥቁሩ ሰው) የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ጋምቤላ ተማረ። ከዚያም ሁለተኛና የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ካናዳ ተከታትሎዋል። በመጀመሪያ የጋምቤላ ልማት ኤጀንሲ (GDA) የሚባል ድርጅት አቋቁሞ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነበር፡፡ በኋላም በጋምቤላ የዛሬ 9ዓመት አካባቢ ከ400 በላይ አኙዋኮች ሲጨፈጨፉ ህይወቱ ተቀየረ፡፡ ሁኔታው በአመለካከቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በግል ህይወቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አመጣ፡፡ ሁሉንም ትቶ ድምጽ አልባ ለሆኑት ድምጽ ለመሆን የአኙዋክ የፍትሕ ምክርቤትን በማቋቋምና በኃላፊነት በመሥራት የመለስ አገዛዝን እና የወንጀሉን ተዋናዮች በዓለምአቀፍ ፍርድርቤት ሊያስከስስ የሚችል ተግባር አከናወነ፡፡ ሆኖም ችግሩ የአኙዋክ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ መሆኑን በጥልቅ ከተረዳ በኋላ ኢትዮጵያ ነጻ ሳትወጣ አኙዋክ ብቻ ወይም ሌላው እንዲሁ በግሉ ነጻ ቢወጣ ችግሩ ፈጽሞ ሊቃለል እንደማይችል በተረዳበት ጊዜ ትግሉን ቀየረ፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ብትመሠረት የሁላችንም ችግር መፍትሔ እንደሚያገኝ በማስተዋል ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን (አኢጋን) (http://www.solidaritymovement.org/) በማቋቋም የትግሉን መስመር አሰፋው፡፡ “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ መሆን አይችልም” የሚለውን መሪ መፈክር በማንገብ “ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ” እንዲሰጥ በመታገል ዓመታትን አስቆጥሯል – ኦባንግ ሜቶ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር!
ጎልጉል፦ደስተኛ ነህ?
ኦባንግ፦ዘወትር የምመለከተው ወደፊት ነው። የማምንበትን አደርጋለሁ። የማደርገው ሁሉ ለኅሊናዬ ስል ነው። ኅሊናዬን እረፍት የሚነሳ ነገር አላደርግም። ግልጽ ነኝ።ዕቅዴ፣ ሃሳቤ፣ እምነቴ፣ ቀናነትና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ዘወትር ደስተኛ ነኝ። በየቀኑ በርካታ በረከቶች አሉኝ። ይህንን ስል ሃዘን አይሰማኝም ማለት ግን አይደለም። በርካታ ጉዳዮች እረፍት ይነሱኛል። ማንም ለራሱ ብቻ መኖር የለበትም …
ጎልጉል፦በተለይ የሚያስደስትህ ምንድር ነው?
ኦባንግ፦የወገኖቼን ችግር ለመቅረፍ የማደርገው ጥረት ልዩ እርካታ ይሰጠኛል። ሰዎችን ለመርዳት ተንቀሳቅሼ ምላሹ መልካም ዜና ሲሆን ደስታዬ ልዩ ነው። የልፋቴን ዋጋ ስመለከት ቀኑን ሙሉ በደስታ እንዳለቅስ ያደርገኛል። እንዲህ ያለውን እርካታ በሌላ በምንም መንገድ ላገኘው አልችልም። እንዲህ ያለው ደስታ ቀኑ ሁሉ የተባረከ እንዲሆን ያደርግልኛል። በሌላ በኩል ደግሞ …
ጎልጉል፦በተለይ የምትጠላው ምንድነው? ይህንን ጥያቄ የማነሳው …
ኦባንግ፦(…አቋርጦ በመግባት) ተንኮል። ጥላቻ። ድንቁርና፡፡ ውሸት …
ጎልጉል፦የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ድብቅ አጀንዳ አለው የሚል አስተያየት ይደመጣል፤
ኦባንግ፦ለጊዜው አላሰብኩም። ባቋቁምስ? ምንድነው ችግሩ? ማንስ ያገባዋል? ምንም ነገር የማድረግ መብቱ እኮ የኔ የግሌ ነው፤
ጎልጉል፦በየጊዜው የሚነሳ ጉዳይ ስለሆነ ግልጽ እንዲሆን ነው የጠየኩህ፤
ኦባንግ፦ከዚህ በፊት ያስታወቅኩኝ ይመስለኛል። የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ወይም በተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የመሳተፍ ባለመብቱ እኔ ብቻ ነኝ። ማንም አያገባውም። እንዲህ ዓይነት ሌሎችን የመቆጣጠር አዝማሚያ ሊገባኝ አይችልም።በተወለድኩበት ጋምቤላ በመቶሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ሃኪም ብቻ ሲመረመሩ ሳይ አመመኝ። ይህ ሳይበቃቸው ጭፍጨፋ ተከተለ። ይህኔ ማንም ሳይቀሰቅሰኝ የተገፉና የሚረገጡ ወገኖችን ለመታደግ ማንም ሳይቀሰቅሰኝ ወሰንኩ። ችግራቸውን ይፋ ለማድረግ አደባባይ ወጣሁ። ድርጅት አቋቋምኩ። በህይወት እያሉ የሚያጣጥሩ ሰዎችን መንገድ ላይ እያዩ ጥሎ መሔድ ይቻላል? ሰብዓዊነት ነው? እየሞቱ ያሉ ዜጎችን ለመርዳት፣ የነሱ ስቃይ ይመለከተኛል ብሎ መነሳት ምን ድብቅ አጀንዳ ይኖረዋል? እንዲህ አይነቱን ኋላ ቀርና የቀረ አስተሳሰብ አልወደውም። አጠላዋለሁ። ከየት እንደመጣሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቃል። እኔ የመጣሁት ፍትህ ለተጠሙ ድምጽ ለመሆን እንጂ ለተንኮል አይደለም። ተንኮል ምን እንደሆነም አላውቅም። ድብቅ ነገርም የለኝም። ከማንስ ነው የሚደበቀው?
ጎልጉል፦ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም ሃሳብ የለህም ማለት ነው?
ኦባንግ፦በራሴ ጊዜ ሁሉንም አደርገዋለሁ። ማንም ለኔ ሃሳብና እቅድ ጊዜ አያወጣልኝም። ማድረግ በምፈልግበት ጊዜ ባደባባይ ልክ አሁን እንደምሰራው አደርገዋለሁ። ለሁሉም ነገር የራሴ የጊዜ ምርጫ አለኝ። እኔ በራሴ ሳንባ የምተነፍስ ሰው ነኝ። እኔን በተመለከተ ምን እያደረኩ እንደሆነ በማሰብ የሚጨነቁ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩ እመክራቸዋለሁ። እኔ የራሴን እቅድ ይዤ እየሰራሁ ነው። ሌሎችም የራሳቸውን፣ ያዋጣናል ያሉትን ይስሩ። በቃ!! ተመለሰልህ?
ጎልጉል፦”ለሁሉም ጊዜ አለው” ብለኸኛል፤
ኦባንግ፦አዎ! ለሁሉም ጊዜ አለው። ፍትህ ለጠማቸው ወገኖች በሚቻለው ሁሉ መድረስ ግድ ነው። የሌሎችን ኑሮና ስቃይ መካፈል ሰው የመሆናችን አንዱ መግለጫ ነው።በእውነት፣ በቀጥተኛው መንገድ፣ የተከታዮችን ልብ ሳንሰብር ማገልገል ለማንም የሚተው ሥራ አይደለም፡፡ ሁላችንም ያገባናል። ባገራቸው ጉዳይ ከሚያገባቸው ዜጎች መካከል አንዱ ነኝ።
ጎልጉል፦ብቻህን ትሮጣለህ ይሉሃል?
ኦባንግ፦እንዲህ ያለው ኢትዮጵያን አሁን ካለችበትም ደረጃ እንደገና ወደ ባሰ ኋላ ቀርነት ለሚመልሳት አመለካከትና አስተሳሰብ እንግዳ ነኝ። በነጻነት የማምን ነጻ ሰው ነኝ። ወዳጆቼን ቅር ያሰኛል እንጂ በርካታ ጉዳዮችን ማንሳትና መናገር የምችልበት አጋጣሚዎች ነበሩ። ራሳችንን ችለን ከመስራት ይልቅ ሌላው ላይ መንጠልጠል ምን ጥቅም እንዳለ ሊገባኝ አይችልም። እኔ የምመራው ድርጅት የራሱ መዋቅር ያለው፣የሚሰራውን የሚያውቅ፣ በሙያቸውና በዜግነታቸው ዓላማውን ተቀብለው ያለ አንዳች ጥቅም የሚያገለግሉት ቦርድና ስራ አመራር ያለው ነው። አባላቶቹም በፍቅር ድርጅታቸውን አምነው የሚሰሩ ናቸው። እኔን ብቻውን ይሮጣል የሚሉ ወገኖች የሚያስቀይሙት እንግዲህ እንዲህ ያሉትን፣ የማያውቋቸውን ሰዎች ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ብቻዬን አይደለሁም። አብረውኝ የሚሮጡና በነጻ ከፍቅር ብዛት ከጎኔ ያሉት ወገኖች እጅግ ብዙ ናቸው። ችግሩ እነዚህ አብረውኝ ያሉ ሰዎች በየቦታው መታየት የሚፈልጉ ስላልሆኑ ለአንዳንድ ሰዎች ብቻዬን ያለሁ ይመስላቸዋል፡፡ እና ብቻውን ይሮጣል ይሉኛል፡፡
ጎልጉል፦ድርጅትህ የተለየ መስፈርት አለው?
ኦባንግ፦ በመጀመሪያ “ድርጅትህ” ያልከውን አልቀበልም፡፡ እኔ መሪ ብሆንም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ “የኦባንግ ድርጅት አይደለም”፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ምንም መስፈርት የለውም፤ በፍጹም። እንደሚታወቀው ሥራችን ሁሉ ህጋዊ ነው፡፡ የጥንካሬያችን መሠረትም ይኸው ነው፡፡ ድርጅታችን በአሜሪካ አገር በሕግ የተመዘገበና የመክሰስም ሆነ የመከሰስ መብት ያለው ነው፡፡ ገቢና ወጪያችንንም በየጊዜው በህጋዊ መልኩ ለመንግሥት መ/ቤቶች ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ የወያኔን ሕገወጥነት የምንቃወመው ራሳችን ሕገወጥ በመሆን አይደለም፡፡ እናም ስለዚህ በሕጋዊነት ላይ የጸና አቋም አለን፡፡ ከዚህ ሌላ ግን የጋራ ንቅናቄያችን አገራቸውን የሚወዱ፣ ሰብዓዊነትን የሚያከብሩ፣ የወደፊት ልጅ ልጆቻቸው ህይወት የሚያሳዝኗቸው፣ እነሱ ያለፉበት መንገድ ስህተትና ኋላ ቀር እንደሆነ የተረዱ በነጻነት የሚምኑ፣ በበጎ ፈቃድ፣ በቀናነት፣ በፍቅርና በርህራሄ የሚያምኑ ነጻ ሰዎች የሚቀላቀሉት ድርጅት ነው። (http://www.solidaritymovement.org/)
የጋራ ንቅናቄያችን የያዘው ራዕይ ብቻውን ታላቁ ሃብቱ ነው። ግን ከግብ የሚያደርሱት ሰዎች ይፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ጎሳና የደም ግንኙነት የማያግዳቸው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መስራቾች ናቸው። እኔን ውሰደኝ። ከጋምቤላ ነው የተገኘሁት። ይህ ታላቅ ሃብት ነው ያልኩት ታላቅ ዓላማ ስለገዛኝ እንጂ ከጋምቤላ ጉዳይ ጋር መሮጥ እችል ነበር። የጋምቤላን ጉዳይ ብቻ አንጠልጥዬ ብሮጥ መስበክ የምጀምረው የቀድሞውን ስህተት ይሆናል። ስህተት መድገም ታጋይ ወይም የሰብአዊ መብት ተሟጋች አያሰኝም።
ጎልጉል፦ላቋርጥህና “የቀድሞውን ስህተት መስበክ” ስትል ምን ማለት ነው?
ኦባንግ፦ነብሱን ይማረውና አቶ መለስ ይሰብከው የነበረው ሁሉ ጥላቻ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው እውነት መሠረት ሁሉም የተረገጠ ህዝብ ነው። ሁሉም የተገፋ ህዝብ ነው። የቱን ጠልተህ፣ የቱን ትወዳለህ? መለስ አማራውን ነፍጠኛና የሌላው ህዝብ ሁሉ ጠላት አድርጎ ሰበከ። ኦሮሞውን ጠባብ እያለ ከሌላው ጋር አጣላው። የተጨቆኑ በሚል ብሄር ብሄረሰቦችን ጥላቻ አስታጠቃቸው። በጥላቻ ላይ መሰረት ያደረገው ስብከት ህይወት ቀጠፈ፡፡ አሁንም ሰው እየሞተ ነው። መፈናቀል አስከተለ። አሁንም አልቆመም። ከሰውነት ባህርይ የወጣና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተካሄደ … ብዙ ማለት ይቻላል። ከጥላቻ የሚገኘው ትርፍ እንግዲህ ይህ ነው። ቀደም ባሉት ስርዓቶችም ቢሆን ከዘመን ጋር አብሮ ባለመሄድ ምክንያት በርካታ ችግሮችን ለማሳለፍ ተገደናል። እናም ይህ አስነዋሪና ኋላ ቀር ፖለቲካ አንድ ቦታ ላይ መቆም ይገባዋል። የምናስቀረው ደግሞ እኛ የዚህ ዘመን ሰዎች ነን። ጥላቻን መስበክ መቆም አለበት። ይህንን ለመረዳት የሚያስፈልገው ቀና መሆን ብቻ ነው። በቀናነት ብቻ ብዙ መራመድ ይቻላል። ቀና ስንሆን ብዙ ነገር ይገለጥልናል። በሁሉም መንገድ ተሞክሮ አልሆነም። ቀና በመሆን ግን ይቻላል።
ጎልጉል፦አቶ መለስ በህይወት እያሉ ስለተጨቆኑና ስለተረገጡ ህዝቦች ሲሉ መታገላቸውን በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር። ባንተ አመለካከት ዋናው ስህተታቸው ምኑ ላይ ነው?
ኦባንግ፦አቶ መለስ ህወሓትን ከፊት አድርገው አዲስ አበባ ሲገቡ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ አድርገው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ተገፍተን በስደት ያለን ሁላችን በየሙያችን አገራችንና ወገኖቻችንን እናግዝ ነበር። የሆነው ግን የተለየ ነው። መለስ “እነሱ” ብሎ ሌሎችን በመወንጀል ጥላቻን ማወጅ ጀመረ። ትውልድን የሚያንጽ ብሄራዊ ሚዲያ ሳይቀር የጥላቻና የቂም ስብከት እንዲያስተጋባ ተደረገ። የዚህ መዘዝ ዛሬ ላይ ጣለን። የጋራ ንቅናቄያችን “እነሱ” የሚል ቋንቋ የለውም። ስንጀምር “እኛ” ብለን ነው። ይህ ልዩ ያደርገናል። የሰው ልጆች ጥላቻን ለመሸከም አይመጥኑም። ጥላቻ የሚዘራብን እንደሰው ስለማንታይ ነው። እንደ ሰው ስላልተከበርን ነው። ሰው መልካም ነገር እንዲያደርግ ከፈጣሪ የተሰጠው ልዩ ስጦታ አለው፡፡ መለስ ግን ይህንን ረስቷል። በብሄር ብሄረሰብ ስም ሲምል ሁላችንንም ሳያሳፍር ነው። ብቻውን ወይም ጥቂት ሰዎች ይዞ ወደ ጥፋት ሄደ፤
ጎልጉል፦ “መሳፈር” ብታብራራልኝ?
ኦባንግ፦በምሳሌ ልግለጸው። ምሳሌው ለመለስ ብቻ አይደለም። ለሁላችንም የሚሆን ነው። አውሮፓና አሜሪካ ወይም ባደጉት አገሮች ተማሪዎች የጉብኝት ጉዞ አላቸው። ለጉብኝት ሲነሱ አውቶቡስ ይቀርባል። አወቶቡሱ እንደቀረበ ቀድመው የሚገቡት ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎች ገብተው ሲያልቁ አስተማሪዎቹ ይቆጥሯቸዋል። ሁሉም መግባታቸውን ካረጋገጡ በኋላ አስተማሪዎቹ ተሳፍረው ሾፌሩን አውቶቡሱን እንዲያንቀሳቀስ ይነግሩታል። አስተማሪዎቹ ተማሪዎቹን ቅድሚያ ሰጥተው ማስገባትና የተባለው ቦታ ድረስ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው። ጉብኝቱም ካለቀ በኋላ ሁሉም  ተማሪዎች አውቶቡስ ውስጥ ተመልሰው ሳይገቡ አውቶቡሱ ዝም ብሎ አይነሳም። ሁሉም ተማሪዎች መኖራቸውና ማንም እንዳልቀረ ደግመው ደጋግመው ያረጋግጣሉ። እንደመጀመሪያው ሁሉም ተማሪዎች መሳፈራቸው ሲረጋገጥ አውቶቡሱ እንዲንቀሳቀስ ለሾፌሩ ያስታውቃሉ።
ጎለጉል፡- ታዲያ ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ምንድነው?
ኦባንግ፡- የምንማረውማ አውቶቡሱ አገር ነው። ተማሪዎቹ ህዝብ ናቸው። እንግዲህ መለስ አገር ሲመራ ሁላችንንም ቆጥሮና መሳፈራችንን አረጋግጦ መሆን ሲጋባው ብቻውን ተሳፍሮ ሌሎች የሚፈልጋቸውን ጨምሮ ቆለፈብንና ብቻውን ነጎደ። አንዳንድ የሚጠቅሙትን ከጎኑ አደረገ። በመሪያችን ያልተቆጠርን በዛን። አታስፈልጉም የተባልነው በለጥን። የተቆለፈብንና የጉዞው ተመልካች የሆን ከልክ በላይ ሆንን። መለስ ካለፉት ስርዓቶች ትምህርት ተምሮ ጉዞውን አንድ ላይ በእርቅና በፍቅር ሊያደርገው ይችል ነበር። መለስ ተገፍቻለሁ ብሎ በረሃ ገባ። ከበረሃ ሲመለስና መሪ ሲሆን እኔንና እኔን መሰል ወገኖችን ገፋንና ከአውቶቡሱ ውጪ አደረገን። ሳንቆጠር የቀረን በሙሉ ሌላ አውቶቡስ ፍለጋ ተሰደድን፤ አሁንም እየተሰደድን እንገኛለን፡፡ በመለስ አውቶቡስ የሚቆጥረን ስላልነበረ ሌላ የሚቆጥረን እንፈልጋለን፡፡ ዛሬም ተመልሰን ይህንን ለመድገም መስራት ያለብን አይመስለኝም። አንዱ ሌላውን እየገፋ በበቀል ታሪክ መሄድ መቆም አለበት። ይህ የእኛ ትውልድ ቢያንስ ቢያንስ ይህንን ማድረግ አለበት። መለስ አልቆጠረንም ብለን የራሳችንን አውቶቡስ ይዘን ከመሄድ ይልቅ መጀመሪያ ወገናችንን እንሰብስብ፤ እንቁጠር፡፡ በተራ ብልጣብልጥነትና በተንኮል ሳይሆን በቀናነት!! ቀናነት!! ቀናነት!! …
ጎልጉል፦እዚህ ላይ አቶ መለስን ብቻ ተጠያቂ እያደረክ ነው?
ኦባንግ፦እሳቸው ይህንን የጥላቻ ታሪክ መቀየር ይችሉ ነበር። መገፋትና መጨቆን አግባብ አይደለም ብለው የታገሉትን ወንድሞችና እህቶች ሞት ሊያከብሩት ይገባ ነበር። “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ” ብለው ባይነሱ ኖሮ የኢትዮጵያ መከራ ያቆም ነበር። በየመን፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በኬኒያ፣ በደቡብ አፍሪካና በተለያዩ አገራት በስደት የሚማቅቁ ወገኖች የመለስ ስርዓት ውጤቶች ናቸው። ድህነት ከፍቶ ቆሻሻ መብላት የጀመሩ ትውልዶች የታዩት፣ በባህር ላይ ሲሰደዱ የሚያልቁ ወገኖች፣ በሲና በረሃ የሰውነት ክፍላቸው እየተወሰደ የውሻ ሞት የሚሞቱት ወገኖች፣ የድርጅት አባል ካልሆናችሁ ስራ አታገኙም ተብለው በረሃብ የሚጠበሱ አካሎቻችን የመለስ ስርዓት ውጤቶች ናቸው። መለስ መነጋገሪያ ይዞ የተናገራቸው የጥላቻና እርስ በርስ የሚያባላ ቅስቀሳ እኔ መድገም አልፈልግም።ማናችንም ልንደግመው አይገባም። በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ራሱ የሁሉም ነገር መሃንዲስ መለስ እንደሆነ አሁን እያረጋገጠ ነው። እኔ የምለው ግን በቀል የሌለባትን አገር ለመመስረት እናተኩር ነው እንጂ መለስን በመውቀስና በመደብደብ ለውጥ አይመጣም። ጥላቻውን ማስተጋባት ከቀጠልን የቀድሞው ስህተት ምሩቃን እንሆንና ምንም በማያውቀው በመጪው ትውልድ፣ በልጅ ልጆቻችን ላይ የምንፈርድ እንሆናለን።ይህንን ካደረግን ከነመለስና ከሌሎች በምን እንሻላለን ለሚለው ጥያቄ መልስ የለም። አርቆ መመልከት አግባብ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው።
ጎልጉል፦ስጋት አለህ ማለት ነው?
ኦባንግ፦እኔ ብቻ ሳልሆን አብዛኛው ህዝብ፣ በተለይም ወደ የትኛው አቅጣጫ እንደሚሄድ መወሰን ያልቻለው ህዝብ ጭንቀት ውስጥ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። ጎጆ ቤት ስትገባ ጎንበስ ማለት አለብህ። ኢትዮጵያችን ዙሪያውን ምስጥ በበላው እንጨት የቆመ ጎጆ ተደርጋለች። የከፋቸው ብዙ ናቸው። ተገደው ሳይወዱ በሃይል የሚመሩ የጥላቻ ፖለቲካ ውጤት የሆኑ ጥቂት አይደሉም። በእንዲህ አይነት ጎጆ ውስጥ ለመግባት በጣም ጎንበስ ማለት ግድ ነው። አለበለዚያ አንዱ እንጨት ከተነካ ጎጆዋ ጎጆ መሆኗ ይቀራል። ይህ አርቀህ ስታይ የምትመለከተው ገጽታ ነው። ይህቺ ጎጆ ጎጆ መሆኗ ከቀረ ቢሮጥም መድረሻ የለም። ጎጆዋን የበላት ምስጥ ጥላቻ ነው። ይህንን ጥላቻ ስናስወግድና በሰብዓዊነት መሰረት ላይ ተተክለን መንቀሳቀስ ስንችል ጎንበስ ሳንል ደረታችንን ገልብጠን ብንገባም የማይነቃነቅ ቤት ይኖረናል። ያቺኑ በቋፍ ላይ ያለች ጎጆ በመጠጋገን ለመኖር ማሰብ በኔ እምነት ኋላ ቀርነት ነው። ራዕይ አልባ መሆን ነው። የአውሬ አስተሳሰብ ነው። ተራ የእሳት አደጋ ወይም የአምቡላንስ አገልግሎት አይነት ነው። እና …
ጎልጉል፡- ምሳሌዎች ሁሉ ይገርማሉ፤ ቅድም ስለ አውቶቡስ ስትናገር ነበር አሁን ደግሞ ጎጆ …
ኦባንግ፡- (በማቋረጥ) ልክ ነህ ለኔ ትልቅ ትርጉም ስላላቸው ነው፡፡ … እና ወደ ጀመርኩት ሃሳቤ ስመለስ … ራሴን በርካታ ጥያቄዎች እጠይቃለሁ። የማገኘው መልስ ይገርመኛል። የኢትዮጵያ ልጆች ደንቆሮዎች ነን እንዳልል፣ በመላው ዓለም ታላላቅ ባለሙያዎች አሉ። ደሃ ነን እንዳልል፣ ሃብት አለን። ታሪክ አልባ ነን እንዳልል፣ የታላላቅ ታሪክ ባለቤት ነን። ባህል አልባ ነን እንዳልል፣ አስገራሚ ባህሎች ባለቤት እንደሆን እረዳለሁ። ታዲያ ችግራችን ምንድነው? እስራኤል ታናሽ ህዝብ ነው። ግን የት ደርሰዋል? እኛ ለምን? ምንድነው የጎደለን? መሪ የሚባሉት ሰዎች በልተው ሌላው ጦሙን ሲያድር ምን እርካታ ይሰማቸዋል? አገር እየሳሳች ስትሄድ በጋራ መፍትሄ እንፈልግ፣ በጋራ እንስራ፣ አንድነታችንን እናጠናክር፣ እጅ ለእጅ እንያያዝ፣ በግሌ የማገኘው ነገር ይቅርና ቅድሚያ አገሬን ለማለት ያልቻልነው ለምንድነው? ይህ ስጋት የኔ ብቻ አይሆንም። ሁሉም ራሱን መጠየቅና ለህሊናው ታምኖ አቅጣጫውን ማስተካከል አለበት። በግልጽ የአመለካከት ለውጥ ማካሄድ አስፈላጊ ነው። የጋራ ንቅናቄያችን ይህንን ጥሪ ማስታላለፍ ይፈልጋል። ማስተዋልና አመዛዝኖ መጓዝ፣ የራስን ስራና የራስን ድርሻ መስራት፣ ሌላውን አለመረበሽ፣ አለመተንኮስ፣ ተንኮል አለመስራት፣ ከሁሉም በላይ ራስን ማክበርና ለሌላው ስቃይ መታመም ያስፈልጋል።
ጎልጉል፦መሪ የመሆን እቅድ አለህ?
ኦባንግ፦ጥሩ መሪ ሊኖረን እንደሚገባ አምናለሁ። ጥሩ መሪ ያስፈልገናል። የራሱን ጎሣ ወይም ወገን ብቻ ሳይሆን ሁላችንም አውቶቡሱን መሳፈራችንን፣ ሁላችንም መቆጠራችንን ካረጋገጠ በኋላ አውቶቡሱ ውስጥ ገብቶ በሩን የሚዘጋ መሪ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነት መሪ ሲኖረን (ስንመርጥ) ሲና በረሃ መታረድ ይቆማል። በባህር የሚጠፋው ነብስ ባገሩ አምራች ይሆናል። የተሻለች አገር ለመፍጠር ግን ዝምታ፣ አያገባኝም፣ የለሁበትም ማለት አይሰራም። ጥላቻን መስበክ ፈጽሞ ወደዛ አያደርስምና ሊታሰብበት ይገባል። አገራችን ከያቅጣጫው እስካሁን የተዘራባት ጥላቻ ይበቃል። አስተሳሰባችንን ቀይረን ከሰራን አገር ቤት ውስጥ ትክክለኛ መሪ እናገኛለን። ስለመቀመጫና ስለ መሪነት ያለን አስተሳሰብ ይህ ነው። የመሪ ችግር አለብን። ጦሟን አድራ ልጆቿን እንደምትመግብ እናት ለሚመራው ህዝብ የሚጨንቀው መሪ ለማየት ደግሞ ሳልሰለች የወደፊቱን እያየሁ እሰራለሁ። እንሰራለን።
ጎልጉል፦እናት ስትል ስለ አያትህ እያነሳህ የምትናገረውን አስታወሰኝ …
ኦባንግ፦(አሰበ፤ ከቆይታ በኋላ) አያቴ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት። መቼም ቢሆን የማልረሳው ዘር ዘርታብኛለች። በሷ ዘመን ሳትማር ስለትምህርት አስፈላጊነት መክራኛለች። አሳስባኛለች። በቃል ብቻ አይደለም ቢጫ እርሳስና 32 ሉክ (ገጽ) ያለው ደብተር ገዝታ ወደ ትምህርት ቤት እንድሄድ አድርጋለች። ህጻን በነበርኩበት ወቅት ሌሎችን ስለማክበር፣ ስለመውደድ፣ ስለመንከባከብ፣ ከጨለማ ውስጥ በመውጣት ለራሳችን ብርሃን ማብራት እንዳለብን ደጋግማ ትነግረኝ ነበር። አሁን ሳስበው የአያቴ ምክርና ተግባራዊ ድጋፍ እዚህ እንዳደረሰኝ ይሰማኛል። ሳስባት በረከት ይሞላኛል።
ጎልጉል፦የምክራቸው መነሻ ምን ነበር? የትምህርትን አስፈላጊነት ለመረዳት የረዳቸው የተለየ አጋጣሚ ነበር?
ኦባንግ፦ቤተ ክርስቲያን ታዘወትር ነበር። በተፈጥሮ ብልህና አዋቂ ናት። ለማወቅ የግድ ዶክተርና ተመራማሪ ወይም መሃንዲስ መሆን አያስፈልግም። ደጋግሜ የምናገረው አንድ ነገር አለ። ሰው ቅን ሲሆን፣ ቅን ሆኖ ለመኖር ሲወስን ብዙ ነገሮች ይታዩታል። በቀናነት የሚገለጽና የሚገኝ ግንዛቤ የሚፈራርስ አይደለም። ቀና ስትሆን ማንንም ለማስደሰት አትኖርም፤ ምክንያቱም ትክክለኛ የሆነ ነገር ብቻ ነው የምታደርገው። ቀና ሰው ባመነበት ሳያስመስል አክብሮና ተከብሮ ይኖራል። ይህ የአያቴ ውርስ ረዳኝ። ከሺዎች ዓመታት በፊት የነበሩትን ኢትዮጵያዊያንና ታሪካቸውን ስንመለከት ከየትኛውም ኮሌጅ አልተመረቁም። ግን አዋቂነታቸው አሁን ድረስ እኛ ልንቀጥልበት ያልቻልነው ነው። የጸዳ ህሊናና ስብዕና ስላላቸው ወገኖች ሳስብ ደስ ይለኛል። አሁን እኔ የማደርገው አያቴ አድርግ ያለችኝን ነው። ነገሮች ተስተካክለው ቢሆኑ ኖሮ እኔ የጸረ ድንቁርናን ዘመቻ አርበኛና አዝማች እሆን ነበር። ድንቁርና ባህላችን እንዳልሆነ አስተምር ነበር። ካገራቸውና ከምድራቸው ሌላ መሄጃ የሌላቸውን ህዝቦችን እንዲገለሉ የሚያደርገውን ቅዠት የሆነና በጣም አስደንጋጭ የሆነ አመለካከት ለማስወገድ እደክም ነበር። ራቁታቸውን የሚሄዱ፣ ጎዳናና ዱር ውስጥ የሚተኙ፣ “ልዩነታችን ውበታችን ነው” እያሉ ለፍቅርና ለአክብሮት ሳይሆን ለቱሪዝም አግልግሎት ገንዘብ መሰብሰቢያ የሚውሉትን አካሎቻችንን የማዳን ስራ እሰራ ነበር። ያ በአገር መስዬ ባስቀመጥኩት አውቶቡስ ውስጥ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ባንድነት ተቆጥረው መሳፈራቸውን የሚያረጋግጥላቸው ስርዓት እንዲገነባ እታገል ነበር። አገር ማለት ህዝብ ነው። በእውነት መምራት ከመሪ ብቻ ሳይሆን አምኖ መመራትም ከተመሪው ህዝብ ይጠበቃል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አግባብነት ያለው ኑሮ ለመኖር ይመጥናል። ሁላችንም የዚህ አለም ስደተኞች ነን። ነጮቹም፣ ሃብታሞቹም፣ ድሃዎቹም፣ ጥቁሮቹም … ህይወታችን ዘላለማዊ አይደለንም። የኮንትራት ህይወት የምንመራ ነን። በዚህ ውስን የኮንትራት ህይወታችን ምንም በማያውቁና ለችግር መንስዔ ላልሆኑ ልጆቻችን የተስተካከለ ዘመን ማውረስ የኛ ግዴታ ነው። ጨለማና ከድንቁርና ውስጥ መውጣት አማራጭ የለውም። አያቴ በዛን ወቅት ይህንን ታስብ ነበር። ይህንን እንዳደርግም ዘርና ጎሳ ሳትለይ ታስጠነቅቀኝ ነበር። በቀናነት!!
ጎልጉል፦የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄም ሆነ አንተ ራስህ ባብዛኛው ስለ “ድርሻ” ትናገራላችሁ። ምን ለማለት ነው?
ኦባንግ፦አዎ! ድርሻ እንላለን። ድርሻ፣ ድርሻ፣ ድርሻ፣ ድርሻ፣ … ድርሻ በማለት ዛሬም ወደፊትም እንጮሃለን። እጅ፣ እግር፣ አፍንጫ፣ ዓይን፣ ምላስ፣ አፍ፣ … ሁሉም ባግባቡ ድርሻቸውን ሲወጡ ሁሉንም የተሸከመው አካል የተሳካ ስራ ይሰራል። ጤነኛም ይሆናል። እግር የዓይን ስራ ልስራ ካለ ችግር ነው። አፍንጫ ምላስ ልሁን ሲል አካል ሙሉ እንቅስቃሴው ይበላሻል። እኛም እንዲሁ ነን። ሁላችንም ድርሻ አለን፤ ድርሻ የሌለው የለም፤ ድርሻችንን ማወቅ አለብን። ድርሻችንን መወጣት አለብን ስንል የማንችለውን ከመስራት በመቆጠብ የምንችለውን ማድረግ ማለት ነው። ሁሉንም ባቅም በእውቀት ማድረግ ማለት ነው። መተማመንና መግባባትን ማስፈን። ለጥቅምና ለጊዜያዊ ደስታ በሚል ሌሎችን በመምሰል ከራስ እውነተኛ ማንነት ጋር አለመጣላት በራሱ የድርሻን መወጣት ነው።
ጎልጉል፦የድርሻን ከመወጣት ጋር በተያያዘ በድርጅትዎ ያስተዋሉት ወይም በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ሊቀየር ይገባዋል የሚሉት ደካማ ጎን አለ?
ኦባንግ፦ስለ ማንኛውም ድርጅት ለይቼ አስተያየት መስጠት አልፈልግም። የምናገረው በጥቅል ለሁላችንም ይሆናል ብዬ የማምንበትን ነው። ወደ ጋራ ንቅናቄያችን ስመለስ ግን ብዙ አስገራሚ ገጠመኞች አሉኝ። በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችን ከስደት ችግር እንዲወጡ አድርገናል። በያሉበት አገርም ህጋዊነት እንዲያገኙ ድርጅታችን ካለው ታዋቂነትና ሕጋዊነት አኳያ ያለአንዳች ክፍያ በነጻ የረዳናቸው እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ ስራችን ብዙ መናገር ባንፈልግም የሚያውቁ ያውቁናል። እንዳንዶች ርዳታ ካገኙና ከችግር ከተላቀቁ በኋላ ተመልሰው እኛው ላይ ዘመቻ የሚያካሂዱ አሉ። ጥላቻን ስለማወግዝና በክፋት አንድ ርምጃ መራመድ እንደማይቻል ስለማምን ወደኋላ ተመልሼ ማሰብና መናገር የማልፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። ዋናው መናገር የምፈልገው ከራስ ጋር የመታረቅና ቀና የመሆን አስፈላጊነት ላይ ነው። በተንኮል ደስተኛ ሆነን አንኖርም። በቀላሉ ተንኮል ባሰብን ቁጥር እያነስን፣ እየቀጨጭን፣ ጭንቀት እየጨመርን እንሄዳለን። ለፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ይህ ለጤናም ጥሩ አይደለም። ጥሩ እንቅልፍ እንኳን መተኛት አንችልም፡፡ ከሁሉም በላይ ሌሎች ከኛ ብዙ የሚጠብቁ ወገኖችን እናሳዝናለን። ትውልድን እናከስራለን። መከራችንን ራሳችን እናረዝመዋለን።
ጎልጉል፦መናገር እየፈለክ የምትጠነቀቅ ይመስላል። ለምን ግልጽ አታደርገውም?
ኦባንግ፦እኔ ነጻ ሰው ነኝ። ማስመሰልና ማድበስበስ፣ ተንኮል፣ ከበስተጀርባ ምናምን የሚባል ነገር አላውቅበትም። እንዲህ ያለውን ባህልም አልደረስኩበትም። ስለማይጠቅም ሞክሬውም አላውቅም። የጋራ ንቅናቄያችን በጀርመን፣ በሜክሲኮ፣ ካናዳ፣ እስራኤል፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ፣ ማልታ፣ ሊቢያ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የመን፣ ዱባይ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጋንዳ … አገርቤት በወያኔ ስርዓት ተገፍተው የተሰደዱ፤ ተቸገርን ብለው ሲጠሩን ካበት ቦታ ጎሳ፣ ብሄር፣ ዘር፣ ክልል፣ ጾታ፣ ማንነት፣ ቀለም ሳንጠይቅ ደርሰናል። የምንችለውን እጅግ ውስን በሆነ አቅም ያለ በቂ ርዳታ አድርገናል። ከሺህ በላይ ወገኖች ከስቃይ እንዲገላገሉ ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲያገኙ አድርገናል። ምንም እንኳ ስደት የሚያስደስት ነገር ወይም ማዕረግ ባይሆንም ከችግር በመላቀቃቸው ደስተኞች ነን። በስደት ካምፕ ውስጥና እስር ቤት ከመማቀቅ መገላገለቸው የበረከት ያህል ያረካናል። የሚያሳዝነው ግን እነዚህ ወገኖች እነሱ ባለፉበት ችግር ውስጥ ሆነው ለዓመታት ለሚማቅቁ ሌሎች ወገኖቻቸው አለማሰባቸው ነው። ያለፉበትን መርሳታቸው ነው። መጀመሪያ እንድረዳቸው ሲጠይቁንና ስናገኛቸው “የጋራ ንቅናቄው የሚያደርገውን አንተም የምትሠራውን እናደንቃለን፤ አባል መሆን እንፈልጋለን፤ አብረን እንሰራለን” ይላሉ። ችግራቸው ሲቃለል ሁሉንም ይረሱታል። ለራሳቸው እንኳን መታመን አይችሉም። በችግራቸው ወቅትና ከችግራቸው በኋላ የማስተውለው ተለዋዋጭ ገጽታቸው ያሳዝነኛል። ቅድም ያልኩት የድርሻ ጉዳይ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። በመከራ ውስጥ ያሉትን ለመርዳት፣ ለስደት መሰረታዊ መፍትሄ ለማምጣት የድርሻን መወጣት አስፋላጊ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። እኛ ሳንረዳዳ ሌሎች አልረዱንም ብንል በጣም ትክክል አይሆንም፤ ከቀልድ አያልፍም።
ጎልጉል፦በአብዛኛው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚያወጣቸው ጽሁፎች እና መግለጫዎች ወደ ሕዝቡ በተገቢው ሁኔታ እንደማይደርስ በአንድ ወቅት ተናግረህ ነበር፡፡ ምክንያቱ ምንድርነው? ችግሩ ያለው የት ላይ ነው?
ኦባንግ፦የጋራ ንቅናቄያችን ማንኛውንም ጽሁፍ ከማውጣቱ በፊት በቂ የሆነ ጥናት ያደርጋል፡፡ በተጠያቂነት የምናምን ስለሆነ ለምናወጣቸው ጽሁፎች ማስረጃ እንሰበስባለን፡፡ ከዚያም ጽሁፉ አስፈላጊ ከሆነ በእንግሊዝኛ ብቻ ወይም በአማርኛ ብቻ ወይም በሁለቱም ቋንቋዎች እናወጣለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሌላ ቋንቋ ለመርዳት የሚፈልጉ ካሉ በራችን ክፍት ነው – ድርሻ የሚለው ነገር በዚህ መልኩ ሊወሰድም ይችላል፡፡ እናም ጽሁፎችን ካዘጋጀን በኋላ ባለን የኢሜይል ሊስት መሠረት በዓለም ዙሪያ እጅግ በርካታ ለሆኑ ግለሰቦች፣ በዳያስፖራም ሆነ አገርቤት ለሚገኙ ለሁሉም የኢትዮጵያ ድረገጾች፣ የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ የሚዲያዎች (ዋና ዋና ለሚባሉት የምዕራብ ሚዲያዎችን ጨምሮ)፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የአርነት ንቅናቄዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ አገር ቤት ለሚገኙ የመንግሥት መ/ቤቶች፣ ባለሥልጣናት እና ቁጥራቸው እጅግ ብዙ  ለሆነ ግለሰቦች እንበትነዋለን፡፡ ድርጅቶችንና ሚዲያን በተመለከተ አይደርሰኝም የሚል ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ጽሁፎቻችን በኢሜይል የማይደርሳቸውና ከሚዲያ መረጃ የሚያገኙ በሙሉ ድረገጾች ላይ ያነባሉ ብለን ስንጠብቅ በርካታዎቹ ጽሁፎቻችን አይለጥፉም፡፡ በፌስቡክ ወይም በኢሜይል ጽሁፋችንን አንብበው በኢትዮጵያውያን ድረገጽ ላይ ሳይለጠፍ በመቅረቱ ግራ ተጋብተው በየጊዜው የሚደውሉልን (ከኢትዮጵያ ድረስ)፣ የሚጽፉልን፣ ምክንያቱን የሚጠይቁ … እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው በጣም እርግጠኛ የሆንባቸውና ወሳኝ የሆኑ ጽሁፎችም ሳይለጠፉ ቀርተዋል፡፡ ምክንያቱን በጭራሽ በማናውቀው ሁኔታ ለረጅም ጊዜ መለጠፍ ያቆሙ ድረገጾችም አሉ፡፡ እስካሁን የነገሩን ነገር የለም፡፡ እኛ ሥራችን ስለሆነ ለታሪክም ስለሚያስፈልግ የምንልከውን ጽሁፍ ማን እንደደረሰውና ማን በማሰራጨቱ እንደተባበረ መረጃ እናስቀምጣለን፡፡ ሳያቋርጡ የሚተባበሩንና ጊዜው ሲደርስ ስም ጠቅሰን የምናመሰግናቸው ድረገጾችና ሚዲያዎች አሉ፡፡ እና ለማለት የምፈልገው ከእኛ በኩል ምንም ችግር እንደሌለ ነው፡፡ ካለ ግን ለመስማትና ለማስተካከል ዝግጁ ነን፡፡
ጎልጉል፦በቅርቡ እስራኤል አገር በእስር ላሉ ወገኖች የጀመራችሁት እንቅስቃሴ በምን ተቋጨ?
ኦባንግ፦የሚቋጭ ነገር የለም። ከእስር የተፈቱ አሉ። ህጻናት ከተማ እንዲገቡ ተደርጓል። ወደፊት በተከታታይ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እንሰራለን። በቅርቡ ዝርዝር ሪፖርት የሚኖረኝ ይመስለኛል። እዚህ ላይ ግን አንድ አስገራሚ ነገር መናገር እፈልጋለሁ። እስራኤል ወገኖቻችን መታሰራቸውን የሰማነው በሚያስደነግጥ ሁኔታ ነበር። በሲና በረሃ የደረሰባቸው ግፍ ማንም ኅሊና ያለውን ወገን ያስደነግጣል።እረፍትም ይነሳል። በማያውቁት የሲና በረሃ ውስጥ አካላቸው በገንዘብ እዳ ሲሰረቅና ሲወሰድ ከመስማት በላይ የወገንን ልብ የሚያደማ ምንም ጉዳይ የለም። ከዚህ መከራ የተረፉትንና በመከራ ላይ ያሉትን ለመታደግ ወስነን ርዳታ ያደርጉልን ዘንድ ሶስት ሺህ የኢሜል መልዕክት በአብዛኛው ለኢትዮጵያውያን አሰራጨን። ምላሽ ያገኘነው ከሰባት ሰው ብቻ ነው። ይህ ያስደነግጣል። ምን ሆነናል? ያሰኛል። በዚህ ላይ ብዙ መናገር አልፈልግም፤ ወደ ሌላ ጉዳይ እንሂድ፤ …
ጎልጉል፦በቅርቡ በኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጥገኝነት ጠያቂዎች ማህበር አመራሮች ጋር እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ጋር ተወያይተህ ነበር፤
ኦባንግ፦የስደት ማመልከቻ ተቀብሎ ከሚወስነው፣ የመጀመሪያ ማመልከቻ ውድቅ ሲደረግ ይግባኝ ሰሚ ሆኖ ብይን ከሚሰጠው፣ ለስደት ማመልከቻ ግብአት ይሆን ዘንድ ውሳኔ መረጃ ከሚያዘጋጀው ላንድ ኢንፎ (Land Info) ከሚባለው ወሳኝ መ/ቤትና በጣም በዝቅተኛ ዋጋ እየሰሩ ጉልበታቸውን ለሚበዘበዙ ተከራካሪ ለመሆን ከሚሰራ ተቋም ጋር ተነጋግረን ነበር። ከሁሉም ጋር ጥሩ የተባለ መግባባት የሰፈነበት ውይይት አድርገን ስለነበር አንድ ለውጥ እጠብቅ ነበር። በግልም መረጃ ልኬላቸዋለሁ። ከውይይታችን አንድ ሳምንት በኋላ ላንድ ኢንፎ ያወጣው አዲስ ሪፖርት የዚሁ ከማህበሩ ጋር በመሆን ያደረግነው ውይይት ውጤት ይመስለኛል። ስራው ተጀመረ እንጂ አላለቀም። ላንድ ኢንፎ በራሱ ድረገጽ፣ በኖርዌጂያን ቋንቋ ይፋ ያደረገው መረጃ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ እኛም በተደጋጋሚ ስንናገረው እንደነበርነው የኖርዌይ መንግስት ዲፖርት ለማድረግ የተስማማው ወገኖቻችን የት እንደሚያርፉ ሪፖርቱ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በራሳቸው ባለሙያና በራሳቸው ቋንቋ የተሰራ በመሆኑ መቀበል የግዳቸው ነው የሚሆነው። በዚህ አጋጣሚ በውይይታችን ወቅት በገቡት ቃል መሰረት ላደረጉት ምስጋና ይገባቸዋል።
ጎልጉል፦በቀጣይ ምን ታስቧል? ምንስ መደረግ አለበት ትላለህ?
ኦባንግ፦በየካምፑ ያሉትን ወገኖቻችንን ሙሉ በሙሉም ባይሆን ከኖርዌይ ጠንካራ አጋሮቻችን፣ ከማህበሩና ከድርጅታችን አባላት ጋር በመሆን ለመጎብኘት ዝግጅት አለን። ሌሎችም ጠንከር ያሉ ስራዎች ይሰራሉ። ቅድም ለማለት እንደፈለኩት ሁላችንም ድርሻ አለን። ማንም አያገባኝም ማለት አይችልም። በኖርዌይ ያሉ ወገኖች አሁን በጀመሩት መንገድ ቢደራጁ ከኖርዌይ አልፈው ሌሎች አገራት ያሉ ወገኖቻቸውን የመጎብኘትና የመርዳት አቅም መፍጠር ይችላሉ። ማህበራቸውን አጠናክረው ቢሰሩ በኖርዌይ እንደማንኛውም ማህበራት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘትና ከተረጂነት መላቀቅ ይቻላቸዋል። መደራጀት ወሳኝ ነው። ይህንን ስል አልሞከሩም ለማለት አይደለም። አባላቶች ሙሉ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ለማሳሰብ ስለፈለኩ ነው። እያንዳንዱ አባል ህግና ደንብ በሚፈቅደው መስራት መብቱን ለማስከበር መስራት ይገባዋል። እጁና እግሩን አጣጥፎ አስቀምጦ ሌሎችን መውቀስ አግባብ አይደለም። የመኖሪያ ፈቃድ ያገኙ ወገኖችም ወንድምና እህቶቻቸውን ለመርዳት፣ ለማገዝ፣ ለመተባበር፣ ለመጎብኘት፣ ችግራቸውን ለመካፈል መነሳሳት አለባቸው። ወረቀት ማግኘት ብቻውን የመኖር ምስጢር አይደለም። የሰው ልጅ ከወረቀት በላይ ነው፡፡ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ ውስጥ የሚገኘው የህይወት ትርጉምና ምስጢር ይበልጣልና!!
ጎልጉል፡- የዕለት ቀንህ ምን ይመስላል?
ኦባንግ፡- በጋራ ንቅናቄያችን የምንሠራው ሥራ ሁሉ ምንም ድብቅ ነገር ስለሌለ ስልኬም ሆነ የኢሜይል አድራሻዬ የስካይፕና የፌስቡክ አካውንቴ ክፍት ነው፡፡ ማንም ሰው በፈለገው ጊዜ ማግኘት ይችላል፡፡ ከዓለም ዙሪያ አለ በሚባለው መገናኛ ሁሉ መልዕክት ይመጣልኛል፡፡ ምስጋና፣ ድጋፍ፣ ዕርዳታ፣ ነቀፋ፣ ስድብ (ወያኔ ከሆኑም ካልሆኑ)፣ የስብሰባ ጥሪ፣ ለምን ይህንን አትሠራም የሚል ትዕዛዝ፣ አስተያየት፣ የፍቅር መልዕክት፣ … ሁሉም ዓይነት ይደርሰኛል፡፡ አብረውኝ ከሚሠሩት ጋር እየተጋራን እናነበዋለን፣ እንሰማዋለን፣ … ይህንን ብቻ መከታተል በራሱ የአንድ ቀን ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ከበርካታ ሰዎች ጋር እገናኛለሁ፤ በየቀኑ የጋራ ንቅናቄያችንን የቤተሰብ መጠን ይሰፋል፤ “ከጎሣ ይልቅ ሰብዓዊነት ይቅደም” የሚለውን በተግባር አይበታለሁ፡፡ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ነገር ፕላን እያወጣሁ አከናውነዋሁ፡፡ በየቀኑ የማደርገውን በዕቅድ አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን በጣም ጊዜ የሚያስፈልገው ነገር መሥራት ካለብኝ ስልኬንም ሁሉንም ነገር ዘግቼ ጊዜዬን ለብቻዬ አሳልፋለሁ፡፡ ያኔ ደውለው ያጡኝንም ሆነ ፈልገውኝ ያላገኙን በሙሉ ይቅርታ እላለሁ፡፡
ጎልጉል፦“ጥቁሩ ሰው” የሚሉህ ለምንድነው? ስሙ ተስማምቶሃል? ወይስ ……
ኦባንግ፦(ሳቀ!!) ቀለሜ ጥቁር ነው። ጥቁር ሰው ነኝ። በትክክለኛው ቀለሜ ተጠራሁ። ቀናህ እንዴ … !? (በፈገግታ ድምጽ)
ማሳሰቢያ፡ – አቶ ኦባንግ ሜቶ ቃለመጠይቁ ያደረገው በአማርኛ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሃሳቡን ለመግለጽ እንግሊዝኛ የተጠቀመበትን ቦታ የቃለምልልሱ ፍሰት ለመጠበቅ ስንል በአማርኛ መልሰን አቅርበነዋል፡፡

Wednesday, 14 November 2012

ፍትህ- የመቀሌው ገረብ ቡቡ የ “አፓርታይድ” መንደር ( በጋዜጠኛ በዮናስ በላይ አበበ (መቀሌ)

በዘመነ መሳፍንት “KING MAKER” (ንጉስ አንጋሽ) ተብለው የተሞካሹ በወቅቱ ..ራስ.. የሚባል ማዕረግ የነበራቸው ቢሆንም ስልጣናቸው ግን በአሁኑ ወቅት ከጠ/ሚኒስትር ስልጣን ጋር አቻ ነው፡፡ ከትግራይ ተነስተው ጎንደር የገቡ ሰው ነበሩ፡፡ እኚህ ራስ የፍትህ ስርዓታቸውም ልክ እንደ መልካቸው እንደነበረ ይነገርላቸዋል፡፡ የሰውየው ሙሉ ስም ራስ ሚካኤል ስሑል እንደሚሰኝ የታሪክ ድርሳናት ይተርኩልናል፡፡ ከራስ ሚካኤል ፍትሃዊ ፍርድ አንዱን እዚህ እንጥቀሰው …..
ከለታት አንድ ቀን የራስ ማካኤል ልጅ ፈረሱ ላይ ያለፍቃዱ የወጣበትን ..ባርያ.. በደም-ፍላት ይገለዋል፡፡ ራስም ይህን ይሰሙና ልጃቸውን ለፍርድ በመኳንንቶቻቸው ፊት አቀረቡት፡፡ ልጁም ስለወንጀሉ ሲጠየቅ ..አዎ.. ገድየዋለሁ.. ብሎ በአባቱ እና በመኳንቶቹ ፊት አመነ፡፡ ብልሁ መሪም መኳንንቱን ..እንግዲያስ ምን ትላላችሁ መኳንንት?.. ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ መኳንንቱም ..ምን አልባት ራስ ሊፈትኑን.. አስበው ይሆናል.. በሚል ጥርጣሬ እርስ በርሳቸው እየተያዩ ያጉረመርማሉ፡፡ ሁሉንም ነገር በትዝብት መልክ ሲመለከቱ የቆዩት ..ሰራሄ ንጉስ..ም፡- ..ምነው ሊቃውንት ሌላ ጊዜ የፍርድ ሃሳብ ለመስጠት ትጣደፉ አልነበር እንዴ?.. ሲሉ በትዝብት ይጠይቋቸዋል፡፡ ከመኳንንቱ መሀል አንዱ እምር ብለው ተነስተው ለጥ ብለው እጅ ይነሱና ..አዎ.. ንጉስ ሆይ.. ልጃችን በደል ፈፅሟል፣ እራሱም በችሎቱ ፊት አምኗል፣ ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው ስህተት እንዲማር ገስፀን፣ ለሟች ቤተሰብ ደግሞ ካሳ ከፍለን ነገሩን ብንዘጋው የተሻለ ነው…. ብለው እንዳመጣጣቸው እጅ ነስተው ሲቀመጡ፤ የተቀሩት መኳንንትም የድጋፍ ድምፃቸውን ሊያሰሙ ተሽቀዳደሙ፡፡ ይህን የተመለከቱት የ..ነብሰ ገዳይ.. አባት ግን በመኳንቶቹ ፍርደ ገምድልነት ልባቸው ተሰበረ፡፡ በመልፈስፈሳቸውም አፈሩ፡፡ እናም ..ታዘብኳችሁ መኳንንት፣ታዘብኳችሁ የዛ ሚሲኪን ልጅ እናት ከዚህ ጥጋበኛ ልጅ እናት በምን ትለያለች? እኔ ግን ያቺ እናት የተሰማትን ሃዘን የልጄ እናትም ትቀምሰው ዘንድ በገዛ ልጄ ላይ ሞት ፈርጄበታለሁ…. ሲሉም ብይናቸውን ተናገሩ፡፡ ይህ ውሳኔያቸው እንዳልፀፀታቸውና ልክ እንደነበር ልጃቸው በፍርዳቸው መሰረት ተሰቅሎ ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ ያገኛቸው አንድ ..ገለልተኛ.. (እንደ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም አገላለፅ) የታሪክ ፀሃፊ ምስክርነቱን ለታሪክ ይሆን ዘንድ ከትቦታል፡፡
…ወታደራዊው የደርግ መንግስት መስከረም 2/1967ዓ.ም ያወጣውን አዋጅ ..ለአምባገነንነቱ እና ለአፋኝነቱ.. እንደ ዋነኛ ምክንያት በመጥቀስ ለትጥቅ ትግል የካቲት 11/67ዓ.ም ወደ ደደቢት ወጡ፡፡ ..ዳግማዊ ወያኔ..ዎች፡፡ እኚህ ..ታጋዮች ራሳቸውን ዳግማይ ወያኔ.. ሲሉ የሰየሙት ከ30 ዓመት በፊት (በ1935ዓ.ም) ገበሬውን የሚበድለውን አዲሱን የመሬት ስሪት አዋጅን ለመቃወም በብላታ ኃ/ማርያም ረዳ አማካኝነት እየተመሩ ያካሄዱት ትግል ..ቀዳማይ ወያኔ.. በመባል ይታወቃል፡፡ …የህወሓት መስራቾችም ከዚህ በመነሳት ነው ..ዳግማይ ወያኔ.. ሲሉ ለራሳቸው ስያሜ የሰጡት፡፡ ይሄ እውነት እንዲህ እንዳለ በቅርቡ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ከ..ቤታቸው.. ወጥተው ወደ ..ጎሳዊነት.. በገቡበት የ..ትግራይ ሽፍቶች.. እያሉ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ስለፃፉት ፅሁፍ አንስተን ከአንድ ..ትልቅ.. መጽሐፍ የፃፈ ሰው ጋር ስናወራ፤ በመሃል አንድ ጥያቄ ወረወረልኝ፤ ..ወያኔ ማለት ግን ሽፍታ ማለት አይደለም እንዴ?.. ሲል፡፡ ደነገጥኩኝ፡፡ ሆኖም ወያኔ ማለት አብዮት ማለት እንደሆነ ግን ከማስረዳት አልቦዘንኩም፡፡ ሽፍታ ፍትህ አያውቅም፣ ወያኔ ግን የፍትህ ታጋይ ነው ለህዝብ የቆመ ስልም መረኩለት፡፡ እንደሚመስለኝ ፕሮፈሰሩ እና ፃሀፊውን እንዲህ በግላጭ ለመሳሳት ያበቃቸው ራሳቸውን ..ወያኔ ነን.. ብለው የሚጠሩት ሰዎች የሚሰሩትን ..የሽፍታ ስራ.. እያዩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ማወቅ ያለባቸው ሽፍታ በህዝብ መካከል እንደሚገኝ ሁሉ በተወሰኑ ወያኔዎችም መካከል ሊገኝ እንደሚችል ነው፡፡ እነሱ ግን በደፈናው ..በሽፍታ.. ስም ሊጠሩ አይገባም፡፡
…በትግራይ ህዝብ ላይ የሚዘንበውን የጭቆና ዝናብ ለማስቆም በእውቀትም ሆነ በስሜት ወደ በርሃ የወጡት ..የቁርጥ ቀን.. ወገኖች፣ ..ወንበዴ.. እየተባሉ፣ በተቆጣጠሩት መሬት (ሓራ መሬት) ዋርካ እግር ስር ሆነው ይሰጡት የነበረ ፍትህ ግን የሽፍታ ሳይሆን የራስ ሚካኤልን ፈለግ የተከተለ እንደ ነበር ዛሬም የአይን ምስክሮች አሉ፡፡ እናም እነዚህ ታማኝ ወያኔዎች በሚሰሩት ስራ የትግራይ ህዝብ አመናቸው፤ ይሄ ሁኔታም ራሳቸው እና ህዝቡ መሰላል ሆኖ ከመካከላቸው ጥቂቶቹን ካሰቡት በላይ በሆነ ወንበር ላይ ሰቀላቸው፡፡ የተቀሩት ..ሻማዎቹ..ም ተስፋ ያልቆረጡ ይመስል፤ አሁንም ድረስ እየነደዱ ያበራሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ከደርግ ቢኤም. እና የጦር ጀቶች ጋር ፊት ለፊት ገጥመው ያሸነፉትና ከድል በኋላ ..የታገሉለት አላማ.. የተቀለበሰባቸው እነዚህ እልፍ አላፋት ታጋይ አንድ ቀን ግን፤ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ጊዜ ለማመን ቀርቶ ለመስማት የሚከብድ ወሬ ከጆራቸው ደረሰ፡፡ የ..አፓርታይድ መንደር በመሀል መቀሌ እየተመሰረተ ነው፡፡..
…መቼም ስለ ..አፓርታይድ ስርዓት.. ያልሰማ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የአፓርታይድ ስርዓትን የአየነውና የሰማነው በአልማዝ መአድን ክምችት በበለፀገችው ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የታላቋ ብሪቲንያ ቅኝ ገዥዎች ባልታሰበ ቀን ተከሰቱ፡፡ መላው ደቡብ አፍሪካንም በመዳፋቸው ስር አስገቡ፡፡ ከዚህ በኋላም ..ነጭ ከጥቁር ይበልጣል.. (White superiority) በሚል ፍልስፍና የተገመደው የአፓርታይድ ስርዓትን በስራ ላይ አውለው፤ ነጭ ባለበት ጥቁር ቢገኝ እስከ ሞት በሚያደርስ ቅጣት ይቀጡ ጀመር፡፡ ይሄ የሆነው በደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ታዲያ ..በትግራይ አፓርታይድ.. ከየት መጣ? የሚል ጥያቄ ካለ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ …ከመሀል መቀሌ በ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ..ገረብ ቡቡ.. የሚባል ኮረብታማ ቦታ አለ፡፡ ማንም ሰው ገረብ ቡቡ ኮረብታ ላይ ሆኖ ሙሉ መቀሌን ጥርት አድርጎ ማየት ይችላል፡፡ ይሄ ኮረብታ ከመቀሌ ከተማ የአየር ፀባይ ጋር በተገናኘ፤ ማስተር ፕላን ወጥቶላት በደን እንዲሸፈን በባለሙያ ተጠንቶ የተወሰነ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ግን መቀሌ በጎርፍና በንፋስ እየታመሰች ዘመኗን ሙሉ ፍዳዋን እያየች እንደምትኖር ተደጋግሞ የተነገረላት ነው፡፡ ይሄ ትንግርት አይደለም፤ በባለሞያ ጥናት የተረጋገጠ እንጂ፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በ1997ዓ.ም ገረብ ቡቡ ድንገት በህወሓት ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ በአመቱም (በ1998) ኮረብታው ላይ የዘመናዊ ቪላ መሰረቶች ተጥለው ታዩ፡፡ ጉዳዩንም ነዋሪው ሲያጣራ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ጥቂት ኢንቨስተሮች (በድምሩ 40 ሰዎች ናቸው) ከመቀሌ ከተማ ነዋሪ የተለየ መንደር ራሱን የቻለ የገበያ ማዕከል፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ የመዝናኛ ማዕከል እና የመሳሰሉትን ተቋማት ያቀፈ፤ በግልባጩ ሌሎች የመቀሌ ሰዎች ድርሻ እንዲሉ የማይፈቀድበት መንደር እየተመሰረተ እንደሆነ ታወቀ፡፡ በዛን ወቅት ማንም ሰው እነዛ ታጋዮች ከ60ሺ በላይ የትግራይ ሰዎች በሞቱለት ድል ተጠቅመወ.. በአፓርታይድ ስርዓት የሚተዳደር መንደር ይመስረታሉ ብሎ አልጠረጠረም፡፡ የሆነው ግን ያልጠረጠረ…
በዚህ ጊዜ እነዛ ታጋዮች፤ እነዛ ሻማዎች ሃይል ያነሰው መብራት መሰሉ፤ ጭለማ ለብሰው ጭለማ ውጠው ሆ ብለው ገነፈለ፡፡ ..ትግራይ የህልውና መሰረቴ.. የሚለውን ህወሓትን አንቀጠቀጡት፡፡ይህንን ጊዜም ጉዳዩ ከአቅም በላይ መሆኑ በመታወቁ ጠ/ሚኒትሩ ውለው ሳያድሩ መቀሌ ገቡ፡፡ እንደደረሱም በሰማእታት ሀውልት ስር ባለው አዳራሽ ስብሰባ ይሁን አውጫጭኝ ያለየለት ነገር ከሹማምነቶቻቸው ጋር ተቀመጡ፡፡ በሁኔታው የተበሳጩ በሚመስል ድምፅ ..ህዝብን ማገልገል፣ አሊያም ከድርጅቱ ወጥቶ ነጋዴ መሆን…. እንጂ እንዲህ አይነት ነገር በጠራራ ፀሐይ አይሰራም ሲሉ በቁጣ ገለፁ፡፡ ካድሬውም ..አይ.. ፍትህ.. በማለት የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ሲያወድስ፤ ሻማዎቹ ግን ..ፍትህማ በዛ በዋርካ ስር ቀረ…. ሲሉ ተቆጩ፡፡ እንደተባለውም አልሆነም ይህ ሃገር ያስቆጣ ነገር፤ በአስተሳሰብ ደረጃ እንጂ በህግ ..ሙስና የሚባል አይደለም.. ብለው ውስጥ ውስጡን ሻማዎችን መሸርሸርም እለቱን ተጀመረ፡፡ በካድሬው፡፡ በመሆኑም ..ጉድ አንድ ሰሞን ነው…. እንደተባለው ሁሉ ይህ ጉድም ተረሳ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ከአንገት በላይ የሆነ ቁጣቸውን አሰምተው ከሄዱ ከወራት በኋላ የአፓርታይድ መንደር ምስረታ በህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቀጠለ፡፡
…ትግራይ በወያኔ ጊዜ ሶስት ንጉሶች አይታለች፡፡ ..አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?.. ያለው ማን ነበር?… ገብሩ አስራት ሄዱ፤ ሃለቃ ፀጋዬ በርሄ መጡ..ሃለቃ ፀጋዬ ሄዱ ሳልሳዊ ንጉሱም ወንበር ያዙ፡፡የመዝገብ ስማቸውም አባይ ወልዱ ይሰኛል፡፡እኚህ ንጉስ ሙስና አይወዱምና ልክ ወንበራቸውን በተረከቡ ማግስት መቀሌ ተተራመሰች፡፡ የሙስና ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆነ፡፡ በተለይ የመሬት ሙስና፡፡ በሃለቃ ፀጋዬ ጊዜ ሙስና ሰሩ የተባሉ ካድሬዎች ከያሉበት ታድነው እስር ቤት ገቡ፡፡ ህገ ወጥ የተባሉ ቤቶችም በገፍ ፈረሱ፤ አላግባብ የተወሰደ መሬትም ተወረሰ፡፡ ከነዚህ ከፈረሱ ህገ ወጥ ቤቶች የአንዱ መንደር አስገራሚ ነበር፡፡ ይህ ሰፈር ገፊሕ ገረብ በመባል ይታወቃል፡፡
እዚህች ጋር ለአፓርታይድ መንደር ጋር ንፅፅር አድርገን መራራውን እውነት እንጨልጣት ዘንድ ስለገፊሕ ገረብ መንደር ጨርፌ ላስተዋውቃችሁ፡፡ …ገፊሀ ገረብ በመቀሌ በስተምዕራብ (የአፓርታይድ መንደር የሚገኘው በስተምስራቅ ነው) የሚገኝ ሲሆን፤ ከመሐል መቀሌም ወደ 6 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች በሙሉ ተፈናቃዮች እና ድሆች ናቸው፡፡ በግምት እስከ 10ሺ የሚደርሱ ቤቶች በገፊህ ገረብ መንደር የመስቀል ደመራን ይመስል ተጨናንቀው ይታያሉ፡፡ ሁሉም ቤቶች የተገነቡት እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጭቃ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም የብሎኬት ቤቶች አሉ፡፡ በዚህች መንደር አንድ ቤተክርስቲያንም ታንፆበታል፡፡ በወቅቱ ቤቶቹ ሲሰሩ የቀበሌ ውል አፈራራሚ ሰራተኞችም በህጋዊ ሰነድ ላይ በመመዝገቡ ተሳትፈዋል፡፡ ይሄ ሲሆን ግን የክልሉ አስተዳዳሪ ሃለቃ ፀጋዬ እያንቀላፉ እንደነበረ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሰውዬው በጭራሽ አላነቀላፉም፡፡ አረ እንዲያውም እንደዚያን ጊዜ ይበልጥ ንቁ የሚሆንበት ወቅት ያለ አይመስለኝም፡፡ ወቅቱ ምን ስለሆነ ነው ብትሉ? መልሴ የ2002 ምርጫ ዋዜማ የሚል ነው የሚሆነው፡፡
እናም በምርጫ ቅስቀሳው አንዱ ቀን ሃለቃ የገፈ ገረብ ነዋሪን ሰብስበው እንዲህ ሲሉ ሸነገሏቸው፡ ..አይዟችሁ፣ ለመሬት ነው እንዴ? እንኳን ለእናንተ ለቅንጅት እስረኞችም ምህረት አድርገንላቸዋል…. በዚህም ድለላ ዳጎስ ያለ የምርጫ ካርድ ሸምተውበታል፡፡ የትኛው ፀሀፊ ነበር ..እንደ ኮንደም ነው የሚጠቀሙብህ…. ያለው?… ከዛማ ምርጫም አለፈ፤ የሃለቃ ፀጋይ ቃልም ታጠፈና፣ እነዚህ ነዋሪዎች፤ ከሌላ አገር የመጣ በሚመስል መንግስት እንደ ሰው ሳይታዩ ቤታቸው በገፍ ፈረሰ፡፡ …የመፍረሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመናገር፣ የመሰብሰብ መብት ከልክለው በህዝቡ ላይ ያወረዱት የዱላ መአት፣ የአስለቃሽ ጋዝ ጢስ፣ የእስር ቤቱ ሰቆቃ… ይህንን ሁሉ በአርምሞ የተመለከተ ..እውነት እነዚህ ሰዎች የመስከረም 2/1967ን አዋጅ በመቃወም ነበር ወደ በርሃ የወጡት?.. ሲል መጠየቁ አይቀርም፡፡ በይበልጥ ደግሞ ያውም ከተማውን ከጎርፍ እና ከንፋስ እንዲከላከል በታቀደው ቦታ ላይ (ገረብ ቡቡ) የአፓርታይድ ግልባጭ የሆነው መንደር ተመስርቶ አይቶ እንዳላየ ባለፈ መንግስት፤ የድሆች ሰፈር ሲፈራርስ፡፡ ምሬቱ አይጣል ነው፡፡
…ማንም ሰው ይህንን ግፍ ሲያይ ትዝ የሚለው የእንግሊዛዊው የጆርጅ ኦርዌል ድርሰት የሆነው ..አኒማል ፋርም.. ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለይ ለህወሓት ሰዎች ቅርብ ነው፡፡ በ1993 ህወሓት ለሁለት ሲከፈል የጠ/ሚኒስትሩ ቡድን ከህወሓት የወጡትን ሰዎች በ..ቦናፓርቲዝም.. ሲከስ እንደ ማብራሪያ የተጠቀመው ይህንን መጽሐፍ ነውና ነው፡፡ እንዳልኳችሁ በአኒማል ፋርም ውስጥ ጉልበተኛ እንስሳቶች በግድግዳው ላይ የፃፉት ማስታወቂያ እንዲህ ይነበባል፡፡
..እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው፤ ግን አንዳንድ እንሰሳት ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው፡፡ ..
በመቀሌ ደግሞ
..ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው፤ ግን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሌሎቹ ይበልጥ እኩል ናቸው…..
እነሆ ሄዶ ሄዶ የትግሉ ውጤት እዚህ ደርሶላቸዋል፡፡…የ..ሙስና ጠላት.. ተብለው የሚወደሱት አባይ ወልዱ፣ ጦራቸው አንድ ቦታ ላይ ሲደርስ እንደተብረከረከም የመቀሌ ህዝብ በትዝብት ተመልክቶአል፡፡ ያ የአባይን ጦር ያንበረከከው ቦታ ገረብ ቡቡ ይባላል፡፡ ስለቦታው ሲጠይቁ፣ ..ቦታው የመሬት ገነት የመሰለ፣ ከዛ ቁልቁል መቀሌን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ኮረብታማ፣ ለከተማው የአየር ፀባይ ተብሎ በማስተር ፕላን በደን እንዲሸፈን የተወሰነ፤ ይህ ካልሆነ ግን መቀሌ በጎርፍና በንፋስ አየታመሰች እንደምትኖር….. የተነገረለት መሆኑን ደግሞ ሲሰሙ ነገሩ ገባቸው እና ካቢኔያቸውን ስብሰባ ጠሩ፡፡ ..እናፍርሰው?..፣ ሲሉ ጠየቁ፡፡ የአፓርታይድ መስራቾችም ..አናፈርስም..፣ ሲሉ በእብሪት መለሱ፡፡ ..ተው ይህ ህዝብ ከሆዱ ካወጣን እንጠፋለን? ብናፈርሰው ይሻላል…. ሲሉም ተለማመጡ፡፡ በዚህ መሃል አንድ የአፓርታይድ መስራች ተነስቶ፣ ..እምቢ.. አላፈርስም ታግዬ ያመጣሁት ነው፤ አላፈርስም…. ሲል ቡራ-ከረዩ አለ፡፡ ቡራ-ከረዩ ብሎም አልቀረ፣ ቤቱን አጠናቆ ገባበት፤ እኔም ይህን ዜና ስሰማ ማየት ማመን ነውና ወደ ገረብ ቡቡ አቀናሁ፡፡ ወደ አፓርታይድ መንደር፡፡ ..ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው…. የሚለውን የወረቀት ህግ ያነበብኩት ቦታ አሁን ትዝ አልልህ አለኝ፡፡ ሁለት ያለቁ ቪላ ቤቶች አየሁኝ፡፡ እየገረመኝ ወደ ማህደረ ካሜራዬ ላኳቸው፡፡ ከአስር የማያንሱ ቪላ ቤቶች ደግሞ እየተፋጠኑ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር የአንድ ወዳጄ ፕ/ር አባባል ትዝ ያለኝ፡፡ ..ትግል ማለት እኮ ቢዝነስ ነው፡፡ አስራ ሰባት አመት ታግለህ እንዲህ የናጠጥክ ሚሊየነር የምትሆን ከሆነ ቢዝነስ ነው.. ያውም ጥሩ ቢዝነስ.. ቢዝነስ.. .. ተብከነከንኩ፡፡ እነዚያን ሰማእታቶች በአየነ ህሊናዬ አሰብኳቸው፡፡ ይህን ቢያዩ ምን ሊሉ ይችሉ ይሆን? በአፅማቸው እና በትግራይ ህዝብ እየተደነገደ መሆኑን ሲሰሙስ ምን ይሉ ይሆን? ….መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች፡፡
እንዴት ለህዝብ ነው የታገልኩት የሚል ሰው ከህዝብ ተነጥሎ መኖር ይመኛል? ለዛውም ላይና ታች፡፡ እንዴትስ ህዝብ የሚጎዳ ነገር ይሰራል? ለዛውም የህልውና ጉዳይ፡፡ ከህዝብ አፍ የሚነጥቁ ፊውዳሎች ይውደሙ ብሎ የተነሳ ሰው እንዴት ራሱ ፊውዳል ሆኖ ቁጭ ይላል? እነዚህ ሁሉ ዛሬም በትግራይ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በቃ.. ማንም ወደ ስልጣን መውጫ መንገድ ሲጨልምበት ነው ይህን ሻማ የሚጠቀምበት? እስከ መቼ ነው ግን ይህ ህዝብ ..መሳሪያ.. ሆኖ የሚያገለግለው? መልሼ ደግሞ ታድያ እንዴት ይኑሩ እያልኩኝ ነው? እነሱስ የሚጠማ ጉሮሮ የሚራብ ሆድ አልያዙምን? እነሱስ መጠልያ አያስፈልጋቸውምን? ብዬ ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ገብረመስቀልና ገብሩ፡፡
ገብረ መስቀል በክፍፍሉ ጊዜ የእነተወልደ ቡድን ተብሎ ከሚጠራው ጎራ የነበረ ነባር የህወሓት የአመራር አባል ነው፡፡ ይህ ሰው ተማሪ እያለ የሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ጓደኛ የነበረ በመሆኑ ትግሉ በድል ተጠናቆ ከበረሃ እንደገባ ሼኩ ደጋግመው ..ምን ላድርግልህ?.. ሲሉ ይወተውቱታል፡፡ ገብረመስቀልም ምንም እንደማይፈልግ ደጋግሞ ይመልስላቸዋል፡፡ አንድ ቀን ግን ሙሉ ሳምሶናይት ገንዘብ (የዶላር፣ እና የፓውንድ ቅልቅል) ይመጣለታል፡፡ ሚስኪኑ ገብረ መስቀል ይህን ብዙ ገንዘብ ተቀብሎ ቤት አልሰራበትም፣ መኪናም አልገዛበትም፡፡እናስ የት አደረገው? ቀጥ ብሎ ወደ ድርጅቱ (በሱ አነጋገር ..ንውድበይ..) በመሄድ ያስረክባል፡፡ …ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ የነመለስ ቡድን የእነ ተወልደ ቡድንን እንዳገደ፤ ይህ ይሆናል ብሎ ያላሰበው ምስኪኑ ገብረ መስቀል የአእምሮ መታወክ ገጠመው፡፡ እናም የሚያሳክመው አጣ፡፡ ያ..ተራራን ያንቀጠቀጠው.. ታጋይ አእምሮውን ስቶ ሙሉ በሙሉ እንደተቃወሰ ተሰቃይቶ ህይወቱ አለፈ፡፡
በዚህን ወቅት ከእነ ተወልደ ቡድን ነጥሎ አቶ መለስ ያነጋገሩት ሌላው ሰው ደግሞ፤ ገብሩ አስራት ይባላል፡፡ መለስ ገብሩን ወደ እራሳቸው ቡድን ለመመለስ አበክረው ስለፈለጉ ..ገብሩ ተው.. እነሱ የያዙትን ይዘዋል አንተ ግን ትጎዳለህ፡፡ ማሃረምህን አንጥፈህ ነው ወደ መለመን የምትገባው..? አሉና በነባሩ ማስፈራሪያቸው የገብሩን አቋም ተፈታተኑት፤መለስ ዜናዊ፡፡ ..ታጋይ እኮ ነኝ…. ሲልም ገብሩ መለሰ፡፡ ይህ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ለህዝብ የታገለ፣ በህዝብ ድጋፍ እዚህ የደረሰ ህዝብ ያኖረዋል፡፡ እኔ ወያኔ እንጂ ሽፍታ አይደለሁም ማለቱ ነበር፡፡ አቶ ገብሩ፡፡ እንደነዚህ አይነት ወያኔዎቸም አሉ፡፡ እነዚህ ከወጡ በኋላ ነገረ ስራቸውን አወቅን እንጂ ስንት ምርጥ የህዝብ ልጆች በድርጅቱ ውስጥ እንዳሉ አምናለሁና፤ እንክርዳዱን ከስንዴው መለየት ተገቢ ይመስልኛል፡፡ ወያኔውን ከሽፍታው ወይም ከአፓርታይዱ፡፡ለነዚህ ፍትህ ላጓደሉ የትግራይ ሰዎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ በታሪክ ጎማ ወደ ኃላ ተጉዘን የወላጆቻቸውን ተሞክሮ እናካፍላቸው፡፡ …ራስ ስብሓት እየተባሉ የሚታወቁት መሳፍንት ግዛታቸውን በሚያስተዳድሩበት ወቅት አንድ እህታቸው፤ ዝም ብለው ዓይናቸው ያረፈበትን መሬት ሁሉ ከድሃው ህዝብ መንጠቅ ሆነ ስራቸው፡፡ ድርጊቱም እየተደጋገመ ሲሄድ የተማረረው ህዝብ ..ፍትህ ይስጡን..?.. ብሎ ወደ ራስ ይቀርባሉ፡፡ ቀርበው ሲያበቁም ክሳቸውን ያሰማሉ፤ ስለክሱ የተጠየቁ እህታቸውም ድርጊቱን እንደፈፀሙ ያምናሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ራስ ተጨንቀው እህታቸውን ሲመለከቱ፤ እንዲህ የሚል ድምፅ ወደ ጆራቸው ደረሰ ..አልጋው ላይ የለህም እንዴ? ወንድሜ በል እንጂ ፍርድህን አሰማኝ?.. ራስም ወሰኑ፡፡ ..ለእህቴ ያልሆነ አልጋ ድፍት ይበል.. ሁሉም የራስዋ እንዲሆን ፈርጃለሁ.. ብለው ውሳኔያቸውን ተናግረው ፋይሉን ይዘጉታል፡፡ …ይህ ከሆነ ከአመታት በኋላም አንድ ቀን የአድዋው ገዢ ጦራቸውን አሰልፈው፤ ራስን ሊወጉዋቸው እየመጡ እንደሆነ የሰሙት ራስ ስብሓት ህዝቡን ..ክተት…. ብለው ሲያውጁ፤ በፍርደ ገምድልነታቸው አዝኖ ለአመታት ለውጥን በመጠባበቅ የነበረው ህዝባቸውም ..እህትዎን ይዘው ይዋጉ…. ብሎ አንድም ሳይወጣ ቀርቶ፤ ለውድቀት ተዳረጉ፡፡ እናም ልብ ያለው ልብ ይበል…መማር የሚችልም፤ይማር፡፡


ይህ ጽሁፍ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ከ6 ወር በፊት የታተመ ሲሆን አስተማሪነቱን ጥልቅ በመሆኑ እንድታነቡት ጭነነዋል።

Monday, 5 November 2012

የኦሮሞ ፖለቲካ ጉዳይ (ከትናንት እስከ ዛሬ) አቶ ቡልቻ ደመቅሣ


የኦሮሞ የፖለቲካ ጉዳይ በየዘመኑ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ ሲመሏ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ ይህ የሆነው ከአፄ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ በፊት፣ የኢትዮጵያ ነገስታት ኦሮሞን ለማሸነፍ ስላልቻሉ በየጊዜው እየተጋጩ እንደምንም አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ፋዘር አልሜዳ የሚባለው የፖርቱጋል ቄስ በዚህ ጉዳይ በሰፊው ጽፏል፡፡ ነገር ግን አብሮነታቸው እንደ ገዥና ተገዥ አልነበረም፡፡ ከአጼ ልብነድንግል ጀምረው እስከ ንጉስ ሳህለ ስላሤ የነበሩት አፄዎች ሁሉ ኦሮሞን ለማሸነፍ እና ለመግዛት ያላደሩጉት ጥረት አልነበረም፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ጉዳይ (ከትናንት እስከ ዛሬ)
ኦሮሞንና ሀገሩን አሸንፈው ለማስገበር የቻሉት አፄ ሚኒሊክ ብቻ ነበሩ፡፡ እሳቸውም ኦሮሞን ለማሸነፍ የቻሉት ከኦሮሞዎች ቀደም ብለው ከፈረንጆች የጦር መሳሪያ ስላገኙ ነበር፡፡ መሣሪያ ያገኙበትም ምክንያት ከእሳቸው ቀድሞ የነበሩት አንዳንድ አፄዎች ለአውሮፓ መንግስታት “ኢትዮጵያ ብቻዋን ክርስቲያን ሆና በአፍሪካ ውስጥ የምትኖር ሀገር ነች” ብለው የአውሮፓውያን መንግሥታትን ስለለመኑና ስላስረዱ የጦር መሣሪያ ማግኘት ቻሉ፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ሚኒሊክ ሸዋን በሙሉ ለመቆጣጠር ሲነቃነቁ ደብረብርሃን አጠገብ በምትገኘው አብደላ በምትባል መንደር ውስጥ ከጎበና ዳጬ ጋር ተገናኙ፡፡ ጎበና ዳጬም በዚያን ጊዜ በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የሉባና የነበዙ አባ ደክር ወዳጅ የነበሩ፡፡ ከአፄ ሚኒሊክ ለጎበና ዳጬ አንድ ነገር ተናገሩ፡፡ “ወደታች ወደደቡብ እንሂድ፡፡ ወደአቢቹ፣ ገላን፣ ጉለሌ፣ አርሲ አብረን እንዝመት፡፡ አንተ የጋላ ንጉስ ትሆናለህ፣ እኔ የኢትዮጵያ ንጉስ እሆናለሁ ተከተለኝ” አሏቸው፡፡ እንደተባባሉትም ወደታች ወደደቡብ መጥተው የኦሮሞን ጎሣዎች መውጋት ጀምሩ፡፡ ጎበናም ራስ ተባሉ፡፡ ነገር ግን አፄ ሚኒሊክ ለጎበና የገቡትን ቃል ሳይጠብቁ ቀሩ፡፡ ጎበናም ብዙ ጊዜ ከተዋጉ በኋላ እየተዳከሙ ሄዱ፡፡ ነገር ግን የሸዋን፣ የወለጋን (በሰላም የገቡ) እና የከፋን (ከፋም በሰላም ገባ) ኦሮሞዎች ካሸነፉ በኋላ አፄ ሚኒሊክ እራሳቸው ጦርነቱን መምራት ጀመሩ፡፡ ራስ ጎበና በቀየሱት መንገድ ሄደው ሌሎች ያልተያዙትን ሀገሮች ያዙ፡፡ ለምሳሌ ሀረርን፣ ውጋዴንን፣ ሱማሌን፣ ቦረናን ያቀኑት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ (እኔ አቀኑ እላለሁ አንዳንድ ሰዎች ግን “ኮሎናይዝ” አደረጉ ነው የሚሉት፡፡ እውነቱን ለታሪክ ተንታኞች እንተዋለን፡፡) ይህ ታሪክ አፈታሪክ ነው፡፡ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት አፈታሪክ የተፃፈ ታሪክ ያህል ዋጋ አለው፡፡ አሁን ልክ አይደለም ብሎ መከራከር ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞዎች ሁሉ ይህን ያምናሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የታሪኩን እርግጠኛነት የሚያረጋግጠው የራስ ጎበና ሕመም ነው፡፡ (በብስጭት እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚናገሩ የእሳቸው ተወላጆች አሉ፡፡)
እኔ እንደብዙ ወገኖቼ ጎበናን አላብጠለጥልም ሰው ስራ መስራት አለበት፡፡ ቤተሰቡን የሚደግፈው የሰራ እንደሆነ ነው፡፡ አለስራ መኖር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ራስ ጎበና ስራ አግኝተው ቢሰሩም የፈለጉት ሳይሆን ቀርቶ ታመው ሞቱ፡፡ ይሄ ማንኛቸውም መሪ የሚያረገው ነገር ነው፡፡ አንዳንዱ አላደርግም ብሎ ይሞታል፡፡ ግን ብዙ ሰው ሞትን አይመርጥም፡፡ አፄ ሚኒሊክ ጎበናንም ባያገኙ ማሸነፋቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ከአውሮፓውያን ብዙ የጦር መሣሪያ አግኝተዋል፡፡
ራስ ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ያደረጉት ስምምነት ለጊዜው ለኦሮሞ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚሄድ መስሎ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ አፄ ሚኒሊክ ኦሮሞን የገዙበት የባሪያ አገዛዝ ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንዲሄዱ አደረጋቸው፡፡ ኦሮሞ ደርግ ላይ ምንም ተስፋ ስላልነበረው የጀነራል ተፈሪ ባንቴ ፕሬዝዳንት መሆን ምንም አልመሰለውም፡፡ ዶክተር ነጋሶ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ለኦሮሞ የተሻለ መስሎ አልታየውም፡፡ ዶክተር ነጋሶም እራሳቸው በስርዓቱ ባለማመን ረግጠው ወጡ፡፡
ከዚያ በኋላ የአፄ ሚኒሊክን የጦር ኃይል መመከት ያልቻለው ኦሮሞ፣ ገባርነትን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ሆኖም ግን አፄ ሚኒሊክ ከዚያ በፊት ኦሮሞ ይዞት የነበረውን መሬት ማስለቀቅ ስላልቻሉ ኦሮሞ በአፄ ልብነድንግል ጊዜ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይዞት የነበረውን መሬት እንደያዘ ቀረ፡፡ እዚህ ላይ እናስታውስ፡፡ የወሎ አሮሞና ትግራይ ውስጥ ያሉት ራያና አዘቦ ኦሮምኛ ቋንቋቸውን እየረሱ አማርኛ ወይም ትግሪኛ መናገር ጀምረዋል፡፡ በአማራ ክልል ውስጥ ያለው ኦሮሞ ዞን ከተፈጠረለት ለምን የራያና አዘቦ ዞን በትግራይ ውስጥ አልተፈጠረም፡፡ ይኼ የሚያሳየው ሕገ መንግስቱ በተፃፈበት ጊዜ (በ1986 ዓ.ም) ህወሓት የነበረውን ፍጹም የበላይነት ነው፡፡
ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያንስ 35 በመቶ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ሕዝቡም ወደ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ይገመታል፡፡ የኦሮሞ መሬት ስፋቱ 387,000 ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ማለትም ጀርመንን ያክላል ማለት ነው፡፡
ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ በገባ ጊዜ ኦነግ አብሮት ስለነበረ ኦሮሞ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሄደ ሊገመት ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኦነግ አስራ ስድስት አመት ከታገለ በኋላ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር አብሮ ሲመለስ አንድ የፀና ስምምነት ተፈራርሞ የመጣ መስሎ ለኦሮሞዎች ታየ፡፡ ስለዚህ ኦሮሞዎች ለጊዜውም ቢሆን ተረጋጉ፡፡ ነገር ግን ሳይቆይ ኦነግ ወደ ትግል ተመለሰ፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ኦሮሞዎች ኦነግ ፌደራሊዝምን የተቀበለ – መስሎአቸው ስለነበር ካገር በመውጣቱ አዘኑ፡፡ ከዚህ ይልቅ በሀገር ውስጥ ሆኖ ስለሰብዓዊ መብት፣ ስለእኩልነትና፣ ስለዲሞክራሲ መታገል ነበረበት ብዬ አስባለሁ፡፡
ኦነግ ተመልሶ ከአገር ሲወጣ “ኢህአዴግ ውስጥ ገብቼ አባል አልሆንም” የሚለውን ኦሮሞ ሁሉ ‹‹የኦነግ አባል ነህ›› እያሉ በጅምላ ማሰር፣ አንዳንዱን መግደል፣ የእለት ተዕለት ትእይንት ሆነ፡፡ በዚች አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሞቱትን፣ የታሰሩትን መቁጠር አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኔ የኦፌዴን መሪ በነበርኩበት ጊዜ ከትልልቆቹ ስራዎቼ መካከል ዋናው ስለኦሮሞ መሞት፣ መታሰር እና መሰቃየት ለኦሮሚያና ለፌዴራል መንግስታቱ እድፍ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ለማስመሰል የፌዴራል መንግስቱ፣ ኦፌዴንና ኦህዴድ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ስለነኚህ ችግሮች ያጥኑና የጥናታቸውን ውጤት ያቅርቡ ተብሎ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር፡፡ መጀመሪያውኑ ከልብ ስላልሆነ ኮሚቴው ቶሎ ፈረሰ፡፡
ኦሮሞ የገዳን ሥርዓት ለመተው የተገደደው በመንግስት እና በዘመኑ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጦች ምክንያት ነው፡፡ የገዳ ሥርዓት እንዳለ ሥራ ላይ መዋል በአሁኑ ዘመን አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ዘመን ወጣቶች ሁሉ በተወለዱበት ሥፍራ አይቆዩም፡፡ ለስራና ለትምህርት ከተወለዱበት ወጥተው ወደሌላ ስፍራ ይሄዳሉ፡፡ አንዱ ትውልድ ሌላውን ትውልድ በሙሉ ካልተካ የገዳ ሥርዓት አይሰራም፡፡
ብዙ የኦሮሞ ምሁራን የገዳን ሥርዓት የሚወዱበት ምክንያት ሥልጣን ላይ ያለው ትውልድ አዲሱ ትውልድ ለስራ ሲዘጋጅ ቦታውን ለቆ መሄዱ ለዲሞክራሲ ጥሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል በማለት ነው፡፡ ለሁሉም በአሁኑ ጊዜ ማንም በተወለደበት ቦታ ለብዙ ጊዜ ቀጥሎ ስለማይኖር የገዳ ሥርዓት ሃሳቡ ሲፀነስ በሰራበት መልኩ አሁን ሊሰራ አይችልም፡፡
የኦሮሞ ጥንታዊ ሀይማኖት ዋቄፈታ ሲሆን፤ ይኼም ብዙ ሰዎች እንደሚሉት ወይም እንደሚመስላቸው ለፍጥረት መስገድ አይደለም፡፡ ወንዝ አጠገብ፣ ታላቅ ተራራ አጠገብ፣ ታላቅ ዛፍ ስር ዋቄፈታ ማድረግ እንደዚህ አይነት ታላቅ ፍጥረትን ለፈጠረው አምላክ መስገድ ነው፡፡ አማኞቹ እንደሚሉትም እግዚአብሔር ራሱን የሚገልፀው በታላላቅ ፍጥረቶች በኩል ነው፡፡ እዚህ ላይ ስለዋቄፈታ ያነሳሁት ባለፈው አስር ቀን ውስጥ ኦሮሞዎች ቢሾፍቱ ሀይቅ አጠገብ የተለመደውን ኢሬቻ ለማድረግ የተሰበሰበውን ህዝብ (ሶስት ሚሊየን ህዝብ ነበር ተብሏል) ፖሊስ በሀይል በህዝቡ መሃከል ለብሶ የለበሳችሁት ልብስ የኦነግ ባንዲራ ነው በማለት በመደብደብ፣ በመርገጥ እና ልብሳቸውን በማስወለቅ ጭምር ከባድ ጉዳት አደረሰባቸው፡፡ ይሄ አድራጎት በኦሮሞዎች ዘንድ እንደ ታላቅ ሀጢያት እና እግዚአብሔርን እንደ መዳፈር መስሎ ታየ፡፡ ይህ ሥርዓት በጠባዩ ለእነርሱ ሀይማኖታዊ ነው፡፡
የህዝብን ድምፅ የሚሻ፣ ሰላምን የሚፈልግ እና ትብብርን ከህዝብ የሚጠብቅ መንግስት እንዲህ አይነት ፀረ-ባህልና ፀረ-ህዝብ ወንጀል አይፈፅምም፡፡ ለጊዜው ለዚህ አድራጎት የምናየው ምላሽ ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ኦሮሞ ይሄንን አድራጎት ይረሳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ማንም ህዝብ ይህ ቢደርስበት ዝም የሚል አይመስለኝም፡፡ የፌደራሊዝም ፅንሰ-ሀሳብ የተዋወቀው ይህን መሰሉን በደል ለማስቀረት ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ በፌዴራሊዝም ስርዓት የሚያምኑትን የኦሮሞ ምሁራን አቋም የሚፈታተን ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ ከሌላው ህዝብ ሁሉ ተለይቶ እንደባእድና ጠላት እየታየ መኖር ቢመረውም ከቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ተስማምቶ በፍቅር መኖር ይፈልጋል፡፡
የኦሮሞ ጥንታዊ ሃይማኖት ዋቄፈታ ነበር፡፡ አሁንም በዋቄፈታ የሚያምኑ ኦሮሞዎች ቁጥራቸው በጣም ብዙ ነው፡፡ ዋቄፈታ ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና የተለየ የኦሮሞ የጥንት እምነት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ልዩነቶች ቢኖሩም ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ አካል ሆነን በፌዴራሊዝም ሥርዓት እንኖራለን ብለን በቆራጥነት ተነስተናል፡፡ እንዲህ የሚለው ወገን ግን ዛሬ ድምፁ እየተዳከመ ሄዷል፡፡ ህዝብ መናቅ እንደ ቀላል ነገር ሆኖ እየታየ ነው፡፡ ቢሾፍቱ ላይ ለኢሬቻ የመጡትን አማኞች የኦነግን ባንዲራ ለብሳችኋል በማለት ደብድበው ልብሳቸውን የነጠቋቸው ሰዎች ራቁታቸውን ከስፍራው ሲወጡ ታይተዋል፡፡
የኢሬቻን በዓል መንግስት ለምን እንደፈራው አይታወቅም፡፡ ከዚህ በፊት ለዘመናት በየዓመቱ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ አሁን የመንግስት የፀጥታ ሰራተኞች አንድ ቡድን ያደመው ወይም ያዘጋጀው ተንኮል ኖሮ የደረሱበት ነገር ኖሮ ይሆን? አናውቅም፡፡ ጨርሶ ኢሬቻን ለማጉላት አይመስለኝም፡፡
ሌላ የኦሮሞ ቅሬታ አለ፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የመንግስት ብወዛ ተደርጎ ነበር፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የመንግስትን አቅጣጫና ፕላን የሚያመላክቱ ብወዛዎች ተፈፅመዋል፡፡ እዚህ ውስጥ ኦሮሞዎች ምንም ሚና አለመጫወታቸው ብዙ ሰዎችን አስገርሟል፡፡ ከሃገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ 35 በመቶ ከመሆናቸው ባለፈ ምድራቸው እጅግ በጣም ሰፊና ሀብታም ሆኖ ሳለ፤ ዛሬ ለኦሮሞ ህዝብ ዝቅ ያለ ግምት እየተሰጠው ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው? የጥያቄው መልስ ያለው ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ነው፡፡ ኦሮሞ ሙሉ የዴሞክራሲ መብቱን የሚጠይቅበት ጊዜ ቅርብ ነው፡፡ ኦሮሞንና የደቡብ ህዝቦችን ማጥቃትና መናቅ በምንም ዓይነት መንገድ ፍትሀዊ አይሆንም፡፡ የሚመጣው የኦሮሞ ትውልድ እንደዛሬው ትውልድ ዓይናፋርና ዝምተኛ አይሆንም፡፡
ፓርላማ ውስጥ እኔና ጓደኞቼ ለምንድን ነው ኦሮሞ የሚጠመደው? ለምንድን ነው ኦሮሞ እንደ ጠላትት የሚታየው? ብለን ስንጠይቅ መልስ አላገኘንም፡፡ ነገር ግን በሽብርተኝነት ህጉ መሠረት ኦነግን ትደግፋላችሁ በማለት በፍፁም ከኦነግ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች በብዛት ታስረው ዛሬ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃሉ፡፡ ፍርድ ቤት የእነኚህን ሰዎች ጥፋት በጥልቀት ቢመረምር አንድም የሚያስከስስ ስራ አልሰሩም፡፡ አንዳንዶቹ የፖለቲካ ነፃነት ያለ መስሏቸው ህዝብን ለማደራጀት እንዲሁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትምህርት ለመስጠት ሲሞክሩ ያለአንዳች ጥያቄ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ብዙ ቀናት ከማቀቁ በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርቡና ለረጅም ጊዜ እስር ቤት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በቀለ ገርባ የሚባል የኦፌዴን ም/ፕሬዝዳንት እነሆ ያለአንዳች ጥፋት ዛሬ ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃል፡፡ የተያዘው ስለ ሰብዓዊ መብት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የነበሩ ፈረንጆች ስለአነጋገሩት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተፃፈው ታምኖበት ነው ወይንስ አንዳንድ ገር ሰዎችን ለማታለል ነው፡፡ ዜጋ የሚያዝበት ሁኔታ፣ ተይዞ ፖሊስ ጣቢያ የሚቆይበት ጊዜ፣ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ጊዜ፣ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን በቀጠሮ የሚያቆይበት ጊዜ ሁሉ በሕገ መንግሥትና በሲቪልና ክሪሚናል ፕሮሲጀር ኮድ ተጽፏል፡፡ እነኚህ ሕጎች ሁሉ በየቀኑ እየተጣሉ ነው፤ በትንሹ ሳይሆን በብዛት ነው፡፡ ይህን ሁሉ አቶ መለስ ከዕረፍታቸው በፊት ያውቁ ነበር፡፡ እኔ ራሴ ከእኔ ቢሮ ስለሚሞቱት ሰዎች፣ ስለሚያዙ ሰዎች፣ ስለሚታሰሩ ሰዎች፣ ብዙ ጊዜ ለክልሉ ፕሬዚዳንት እና ለጠቅላይ ሚ/ር ቢሮ ጽፌአለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዛሬም በእሳቸው ቦታ የተተኩ ሰዎች በኦሮሞ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ መብት እንዳይደፈር አንድ ወገን ለይቶ ማጥቃት ተገቢ አለመሆኑን የወጣ አዲስ ትዕዛዝ አላየንም፡፡ ለወደፊትም ላናይ ነው?
ማስታወሻ
ከዚህ አጭር ጽሁፍ ጋር አያይዤ ለአንባቢያን የማሳስበው ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ አንድ ጥያቄ ሁልጊዜ ይጠይቁኛል፡፡ “ለምን ሁልጊዜ ስለ ኦሮሞ ብቻ ትጽፋለህ?” መልሶቼ ባያጠግቡም ሁልጊዜ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ “እኔ ደህና አድርጌ የማውቀው ስለ ኦሮሞዎች ስለሆነ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግስትም ኦሮሞን ለይቶ ስለሚያጠቃ ነው፡፡ ሌላውንም ህዝብ አጥቅቷል፡፡ ለምሳሌ ሲዳማና ጋምቤላ በጣም ተመቷል፡፡ ስለነሱ በዝርዝር የሚያውቁት መጻፍ ይገባቸዋል፡፡ እኔ ስለ ኦሮሞ ስጽፍ ኦሮሞ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም በማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ህግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ማንም ቡድን፣ ብሔር ወይም ሌላ ስብስብ መጠቃት የለበትም፡፡ ፌደራሊዝም ስራ ላይ እንዲውል እንደዚህ አይነቱን የተዛባ አመለካከት እና አያያዝ ለመከላከል ነበር፡፡ እኔ ለኦሮሞ የምፅፍበት ሌላ ምክንያት የለኝም፡፡ ግን ሌላም የኢትዮጵያ ጉዳይ ደጋግሜ እጽፋለሁ፡፡